የአርባ ምንጭ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አዲሱን 2015 ዓ/ም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ 2014 ዓ/ም በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት እና ሌሎችም ሀገራዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች በተሻለ ሁኔታ ተከናውነው የተጠናቀቁበት፣ በርካታ የመጀመሪያ፣ 2ና 3 ዲግሪ ተማሪዎች የተመረቁበት ሲሆን ከዚህ አንፃር የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ለተቋሙና ለሀገር ያደረገው አስተዋጽኦ እንዲሁም ለስኬቶቹ  የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ምስጋናና አድናቆት አቅርበዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ አዲሱ 2015 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲያችን፣ ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የትምህርት ማኅበረሰብ እንዲሁም ለሀገራችን ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነት፣ የእድገትና የብልጽግና ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የ2015 አዲስ ዓመት በሀገራችን ጦርነት ቆሞ ሕዝባችን ሰላም የሚያገኝበት፣ ሀገራችን በእድገት ጎዳና የምትጓዝበት፣ ሠርተን የምንለወጥበትና የምናድግበት እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን የእድገት ጉዞ የሚቀጥልበት፣ የ2 እና 3 ዲግሪ መርሃ ግብሮችን የምናስፋፋበት፣ ተገልጋዮቻችንን የበለጠ በማርካት በመማር ማስተማር፣ በምርምርም ሆነ በማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች አፈጻጸምና በአጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ደረጃ የምንደርስበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ በመልካም ምኞት መልዕክታቸው ባሳለፍነው በጀት ዓመት በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ የተቻለው በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ያላሰለሰ ጥረት በመሆኑ ላሳለፍነው ስኬታማ ዓመት በቅድሚያ ሁላችሁንም ለማመስገን እወዳለሁ ብለዋል፡፡

ም/ፕሬዝደንቱ 2015 ዓ/ም መልካም የሥራ፣ የስኬት ዘመንና የተሻሉ ግቦች የሚመዘገቡበት እንዲሁም በ2014 በጀት ዓመት የነበረው የተግባቦት፣ የተነሳሽነትና የመቻቻል መንፈስ በላቀ ሁኔታ የሚቀጥልበት፣ ለሀገራችን ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና ለሕዝባችንም የረፍት ዓመት እንዲሆንና ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆችዋን ይባርክ ዘንድ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወልደመድኅን የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የቀድሞ የዩኒቨርሲቲያችን ምሩቃን እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲሱ ዓመት ያሉብንን ችግሮች ቀርፈንና ተምረን ወደ ፊት የምንሻገርበት፣ በማስተዋል የምንጓዝበት፣ ሀገራችን ከጦርነት የምታርፍበት፣ የሰዎች ችግርና ስደት ቆሞ የከፍታ ጉዞ የሚጀመርበት ዘመን እንዲሆን እየተመኘሁ ፈጣሪ ሀገራችንና ሕዝቦቿን ይባርክልን፤ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን ብለዋል፡፡

መልካም አዲስ ዓመት!!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት