የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በማኔጅመንት፣ በኢኮኖሚክስና በአካውንቲንግ ትምህርት ክፍሎች በ2015 የትምህርት ዘመን አዳዲስ የትምህርት መርሃ ግብሮች ለመክፈትና ነባሮቹን ለመከለስ ጳጉሜ 03/2014 ዓ/ም የ2ኛና 3ኛ ዲግሪ የሥርዓተ ትምህርት የውጭ ግምገማ አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹MA in Human Resource Management››፣ ‹‹MA in Project Management››፣ MA in Entrepreneurship››፣ ‹‹MSc in Financial Economics››፣ ‹‹MSc in Industrials Economics››፣ ‹‹MSc in Natural Resource and Environmental Economics››፣ ‹‹PhD in Agricultural Economics››፣ ‹‹MSc in Investment and Finance››፣ ‹‹PhD in Accounting and Finance›› አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመክፈትና ‹‹MSc in Economic Policy Analysis››፣ ‹‹MSC in Development Economics››፣ ‹‹MSC in Agricultural Economics›› እና ‹‹MSc in Accounting and Finance›› ፕሮግራሞች ሥርዓተ ትምህርት ለመከለስ የውጭ ግምገማው ተዘጋጅቷል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ውጤታማ የድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች በስፋትና በጥራት መኖር የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ መለኪያ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚሠሩ አካላት ለውጤታማነቱ አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ከትምህርት መርሃ ግብሮች ማሻሻል ባሻገር የጥራት ጉዳይ እንደ ሀገር ትኩረት የሚሰጠውና ትክክለኛ ሥርዓተ ትምህርት መኖሩ ውጤታማ መማር ማስተማር እንዲኖር መሠረት በመሆኑ ሥርዓተ ትምህርቶችን በአግባቡ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ በምናዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት ተምረው የሚወጡ ተማሪዎች በገበያ ላይ ያላቸው ተፈላጊነት በትኩረት ሊመዘን ይገባል ያሉት ዶ/ር ዓለማየሁ የግምገማ መድረኩ መዘጋጀቱ ሥርዓተ ትምህርቶቹ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ በእጅጉ ይረዳል ብለዋል፡፡  

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ ከዚህ ቀደም በት/ክፍሉ መምህራን በርካታ የድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮችን ለማስጀመር የልምድ ልውውጦች፣ የዳሰሳ ጥናት፣ ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻና ጠንካራ የውስጥ ግምገማ መካሄዱን አስታውሰው ክለሳ የተደረገባቸው የትምህርት መርሃ ግብሮች አሁን ያለውን የሀገሪቱ የትምህርት ደረጃና ፖሊሲ ታሳቢ ያላደረጉ በመሆኑ ከአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ ከ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድና ከዩኒቨርሲቲው የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር በማጣጣም ለማስኬድ ክለሳው መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ዲኑ በተጨማሪም የድኅረ ምረቃ ትምህርቶችን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ማስፋፋት እንደ ኮሌጅ በ2015 በጀት ዓመት ለማከናወን በዋናነት ከታቀዱ ተግባራት መካከል አንዱ በመሆኑ ይህን ለማሳካትና ስሙን የሚመጥን ተቋም ለመገንባት በትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት መርሃ ግብሮቹ አስፈላጊና ወሳኝ ዘርፎችን ያካተቱ እንዲሁም ጊዜውን በቃኘ መልኩና ምርምርን ትኩረት አድርጎ የተዘጋጁ ሲሆን በኮሌጁ የድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች ወደ 23 ያደጉ መሆኑን ዲኑ ተናግረዋል፡፡

የሥርዓተ ትምህርቱ የውጭ ገምጋሚ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ዝነኛው ዐቢይ በሀገሪቱ የ3ኛ ዲግሪ ምሩቃን እጥረት መኖሩን ጠቅሰው የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ምርምር ተኮር በመሆኑ ለፖሊሲ ቀረጻ ግብዓቶችን ለማግኘት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቶቹ በውጭ ገምጋሚዎች መታየታቸው የተሻለ ልምድ ለመቅሰምና ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት እንዲኖር ይረዳል ያሉት ዶ/ር ዝነኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰል መርሃ ግብሮችን በመተግበር ብቁ ትውልድ ለማፍራት የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ሌላኛው የውጭ ገምጋሚ ዶ/ር አረጋ ሥዩም የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ መድረኮች መዘጋጀታቸው አላስፈላጊና የሀገሪቱን ችግሮች ባላገናዘበ መልኩ የሚቀረጹ ሥርዓተ ትምህርቶችን የሚያስቀርና ሀገሪቱ የምትፈልገውን የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አረጋ ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሸጋገርና የመንግሥት የእድገት ፖሊሲን ለማሳካት የሰው ኃይል ሚና ትልቅ በመሆኑ ያለንን ውስን ሀብት ሳናባክን በተመረጡና ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ በሚችሉ የትምህርት መርሃ ግብሮች ላይ ማዋል ይገባል፡፡

በውጭ ገምጋሚነት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የመጡት ዶ/ር ስሜነህ በሴ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶ/ር ወንድይፍራው ሙሉጌታ በበኩላቸው ለሥርዓተ ትምህርት ግምገማው የቀረቡ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸውና አብዛኛዎቹ በጥቂት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ የሚሰጡ መሆናቸው ዩኒቨርሲቲውን ተመራጭ እንደሚያደርገው ገልጸው በግላቸው ጥሩ ልምድ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል መምህርና የ‹‹PhD in Agricultural Economics›› ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ኮሚቴ አባል ዶ/ር መልካሙ ማዳ መርሃ ግብሩ ሀገራችን እየተከተለች ባለው ግብርና መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ግብርናውን የሚያዘምኑና የዘርፉን ችግሮች የሚፈቱ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የአካውንቲንግና ፋይናንስ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ በበኩላቸው በትምህርት ክፍላቸው በ2 መርሃ ግብሮች ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸው መርሃ ግብሮቹ የኮሌጁን ዕቅዶች ከማሳካት ባለፈ በዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ የጎላ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የት/ክፍል ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን፣ ከሙያ ማኅበራት፣ ከኢንደስትሪዎችና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡


የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት