የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት በሦስት የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብሮች ላይ መስከረም 04/2015 ዓ/ም የሥርዓተ ትምህርት የውጭ ግምገማ አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹MA in Developmental Psychology››፣ ‹‹MA in Educational Supervision and Quality Management›› እና ‹‹MA in Educational Resource Planning and Management›› ለሥርዓተ ትምህርት ግምገማ የቀረቡ የትምህርት መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ እንደገለጹት ጠንካራ የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ መደረጉና የአዳዲስ መርሃ ግብሮች መከፈት ዩኒቨርሲቲው እንደ ተቋም የያዘውን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እንዲያሳካ እንዲሁም ለት/ቤቱ፣ ለተማሪዎች ብሎም ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡

በሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪና የት/ቤቱ ዲን ተወካይ አቶ ሙሉቀን ተስፋዬ በበኩላቸው ሥርዓተ ትምህርቶቹ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ልምድና ተሞክሮዎችን በመቀመር መዘጋጀታቸውን ገልጸው በውጭ ግምገማው ከትምህርት ሚኒስቴርና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት PhDና ከዚያ በላይ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሉቀን የውጭ ግምገማ መደረጉ ከሌሎች ተቋማት ልምድ በመውሰድ የመርሃ ግብሮቹን ጥራት ከመጨመር ባሻገር በገበያ ላይ ተፈላጊ ለመሆን ያግዛል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ስርጸት ባለሙያና የውጭ ገምጋሚ ዶ/ር አቡኑ አረጋ የመርሃ ግብሩ አዘገጃጀት ትክክለኛውን ሂደት መከተሉ፣ ለሀገሪቷና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ያለው ጠቀሜታና መሰል ጉዳዮች በትኩረት መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የተሰጡትን ገንቢ አስተያየቶች አካቶ ከተሠራ የትምህርት ጥራትን የሚያሻሽልና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል በመሆኑ ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለሀገር የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ መርሃ ግብሩ ዘላቂነት እንዲኖረው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው የውጭ ገምጋሚ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አንተነህ ዋስይሁን በበኩላቸው የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው መካሄዱ ጥራት ያላቸው መርሃ ግብሮችን በመክፈት ተማሪዎች በሥራው ዓለም ተፈላጊ ባለሙያ እንዲሆኑና ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሠሩ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሀገሪቷ ለትምህርት የምታፈሰው መዋዕለ ንዋይ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል አለበት ያሉት ዶ/ር አንተነህ ሥርዓተ ትምህርት ሲቀረጽ የሀገሪቱን ችግር የሚፈታና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ምሩቃን የሚወጡበት መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አንተነህ በግምገማው ሥርዓተ ትምህርቶቹ ከዚህ አንጻር ያላቸው ፋይዳ ተፈትሿል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ጥራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን ዳይሬክቶሬታቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከት/ክፍሎች ጋር እንደሚሠራ ጠቅሰው በቀጣይም የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ በሚካሄድበት ጊዜ የመርሃ ግብሩ አካባቢያዊና ሀገራዊ ጠቀሜታ፣ የፍላጎት ግምገማ ማድረግ፣ የሰው ኃይልና አስፈላጊ ቁሳቁሶች መሟላት ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጁ ካውንስል አባላትና የት/ክፍሉ መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

 የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት