Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የ35ኛው ባች 2ኛ ዙር  1,200 ተማሪዎችን መስከረም 12/2015 ዓ/ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 84ቱ በሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን ከአጠቃላይ ምሩቃንም 387ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ታገሠ ጫፎ ባስተላለፉት መልዕክት ለስኬቱ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ተመራቂዎች ለዚህ ትልቅ ስኬት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ ሀገራችንን ለማሳደግና ዕጣ ፈንታዋን ለመወሰን በምንሠማራበት መስክ ሁሉ እጅ ለእጅ በመያያዝ ውጤታማ የሆነ ሥራ መሥራት ከቻልን ሀገራችን ትበለጽጋለች ብለዋል፡፡

አክለውም የመንግሥት ትኩረት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ላይ በመሆኑ ይህንንም ለማድረግ የመምህራንን አቅም መገንባት፣ ቤተ-ሙከራዎችን፣ ቤተ-መጻሕፍትንና ወርክሾፖችን ማደራጀት እንዲሁም በየደረጃው ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ማፍራትና ግብዓቶችን ማሟላት ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሠራት አለበትም ሲሉ አቶ ታገሠ ተናግረዋል፡፡ የዕለቱ ክብር እንግዳ አቶ ታገሠ ተመራቂዎች ራዕይን በመያዝ፣ በሥነ ምግባር በመታነፅና ራስን በመግዛት በሥራው ዓለም በትጋት እንዲያልፉ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን መጪው የሥራና የአገልግሎት ዘመናቸውም ስኬታማ የሚሆኑበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው የ2014 የትምህርት ዘመን የ35ኛ ባች 2ኛ ዙር ተመራቂዎችን ጨምሮ ባለፉት 35 ዓመታት ከ73,000 በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለሀገሪቱ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ማበርከት መቻሉን በመግለፅ ዩኒቨርሲተው በሀገሪቱ ካሉ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በመሆኑ የምርምር ዘርፍንና የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ አክለውም ምሩቃን ከዩኒቨርሲቲው በገበያችሁት ዕውቀትና ክሂሎት በየተሠማራችሁበት የሙያ መስክ ሁሉ ሕዝባችሁንና ሀገራችሁን በመልካም ሥነ ምግባር በማገልገልና በዩኒቨርሲቲው ቆይታ የካባታችሁትን የሰላም ዕሴት በሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ በማስቀጠል ለሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ቅድሚያ በመስጠት የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ  ሲሉ ያሳሳቡ ሲሆን ለተመራቂዎች መጪው ዘመን መልካም የሥራና የስኬት ዘመን እንዲሆን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እጩ ምሩቃንን ለምረቃ በማቅረብ ያስመረቁ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው የ35ኛ ባች 2ኛ ዙር ተመራቂዎችን  ጨምሮ ወንድ 56,679 ሴት 17,145 በአጠቃላይ 73,824 ተማሪዎችን አስመርቋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ ከኢንስቲትዩቶች፣ ኮሌጆችና ት/ቤቶች ከፍተኛና ከሴቶች የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎችን በማቅረብ የተዘጋጀላቸውን የልዩ ሽልማትና የሜዳሊያ ሽልማት እንዲሁም ሁሉም የሕክምና ዶክትሬት ተመራቂዎች ዲፕሎማቸውን ከዕለቱ የክብር እንግዳ እጅ እንዲወስዱ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ማሌቦ 1,200 ተማሪዎች የሚፈለግባቸውን የመመረቂያ መስፈርት ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት መስከረም 10/2015 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ማጽደቁንም ገልጸዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ተመራቂዎችን ቃለ-መሃላ ያስፈጸሙ ሲሆን አቶ ፍስሃ በቀለ የዕለቱን መርሃ-ግብር መርተዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ የባህል ኪነት ባንድም የተለያዩ ጥዑመ ዜማዎችንና ውዝዋዜዎችን በማቅረብ የዕለቱን መርሃ-ግብር አድምቋል፡፡

ከሕክምና ትምህርት ቤት 3.83 በማምጣት በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ ተማራቂ የሆነችው ዶ/ር መቲ ቶሌራ ለዚህ ስኬት በመብቃቷ የተሰማትን ደስታ በመግለጽ ማንም ሰው በተሠማራበት የትምህርት ዘርፍ በርትቶ በፅናትና በትጋት ከሠራ የላቀ ውጤት ማምጣት ይችላል ብላለች፡፡ በተመረቅሁበት የሕክምና ሙያ አይተኬና ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት በመንከባከብ ያስተማረኝን ማኅበረሰብ በታማኝነት ለማገልገል የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ ያለችው ዶ/ር መቲ ለስኬቷ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ሁሉ ከፈጣሪዋ ጀምሮ ለቤተሰቦቿና ለመምህራኗ ምስጋና አቅርባለች፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባልና የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የጋሞ አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና የሴኔት አባላት ተገኝተዋል፡፡

                                                                                                                                                                                                       የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት