አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቤልጂየም ሀገር 5 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር የሚሠራው “AMU-IUC – Arba Minch University – Institutional University Cooperation”  ፕሮግራም 2 ዙር የኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎና በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር ስቴፋን ቲጂስ/Stefaan Thijis/ በተገኙበት መስከረም 11/2015 ዓ/ም በይፋ ተጀምሯል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ የትብብር ፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲውን የማስተማርና የምርምር አቅም ከማጎልበትና ከመገንባት አንፃር የጎላ ሚና የተጫወተ በመሆኑ  ለቤልጂየም መንግሥት፣ የሀገሪቱ ግብር ከፋዮች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የፕሮግራሙ አካል በመሆን በጋራ ሲሠሩ ለነበሩ የ5ቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲም የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር የሥራ ጊዜ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለተወጡ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ምስጋናቸው ያቀረቡት አፈ ጉባዔው በቀጣይ 2ው ዙር የፕሮግራሙ የሥራ ጊዜ ውጤታማ እንዲሆን በመጀመሪያው ዙር የታየው ቅንጅት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ 

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የ“AMU-IUC” ትብብር ፕሮግራም እ.አ.አ ከ2017-2022 በነበረው የ5 ዓመታት የመጀመሪያ ዙር ቆይታ ዩኒቨርሲቲው እንደ ሀገር ለምርምር ሥራዎች ምቹና ጠንካራ ተቋም እንዲሆን   በተለያዩ የአቅም ግንባታ ዘርፎች ጉልህ ሚና አበርክቷል ብለዋል፡፡ በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር 19 የሀገር ውስጥ መምህራን የ3 ዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ጥራት ለማሻሻልና የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በማስፋፋት የመማር ማስተማር ሥራው ምርምር ተኮር እንዲሆን እያደረገ ለሚገኘው ጥረት አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡ ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው የቀጣይ 10 ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዲያሳካ የፕሮግራሙ 2 ዙር ትግበራም ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር ስቴፋን ቲጂስ/Stefaan Thijis/ በበኩላቸው በቤልጂየም የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ሥራዎች በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረው ዩኒቨርሲቲዎች የአዳዲስ ሃሳቦችና ቴክኖሎጂዎች መነሻ እንደመሆናቸው እነዚህ የትብብር ሥራዎች ዘላቂ ልማትን ዕውን ከማድረግ አንፃር ፋይዳቸው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡ በቤልጂየምና በኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በአቅም ግንባታ፣ በዕውቀት ሽግግር፣ በምርምርና በሰው ኃይል ልውውጥ የተጀመሩ የትብብር ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ እንዲሁም ለተጀመሩና ወደ ፊት ለሚጀመሩ ትብብሮች ውጤታማነትም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡ ዕውቀት ዋጋ የሚኖረው ማኅበረሰብን ሲጠቅም ብቻ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ በመጀመሪያው ዙር የፕሮግራሙ ቆይታ የተገኙ ዕወቀቶች፣ ልምዶችና የምርምር ግኝቶች ተግባር ላይ ውለው ችግርን እንዲቀርፉ መሥራት የፕሮግራሙ የ2ው ዙር ትኩረት እንዲሆን በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

የ “AMU-IUC” ፕሮግራም ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ የትብብር ፕሮግራሙ በስሩ 6 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመያዝ ባለፉት 5 ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው በመጀመሪያው የትብብር ዘመን የተከናወኑ ሥራዎች በገለልተኛ አካላት ተገምግመው ውጤታማ መሆናቸው በመረጋገጡ የ2ው ዙር ዕድል መገኘቱን ገልፀዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የፕሮግራሙ ዘመን 19 የዩኒቨርሲቲው መምህራን 3 ዲግሪ ትምህርታቸውን ቤልጂየም ሀገር በሚገኙ 5 ዩኒቨርሲቲዎች የመማር እና ጥራት ያላቸው የማኅበረሰብንና የአካባቢን ችግር መፍታት የሚያስችሉ፣ አዳዲስ ዕውቀቶችን ከማመንጨት አንፃር ጉልህ ሚና ያላቸው የምርምር ሥራዎችን የማከናወን ዕድል ማግኘታቸውን ዶ/ር ፋሲል ገልጸዋል፡፡ በየ15 ደቂቃው መረጃ ማቀበል የሚችል የሐይቅ ውሃ ጥራት መለኪያ ማሣሪያ፣ አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ ጣቢያዎችና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የምርምር ቤተ-ሙከራዎች በዩኒቨርሲቲው መደራጀታቸውን የፕሮግራሙ ማኔጀር ጠቅሰዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲውን የICT መሠረተ ልማቶች የማጎልበት ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ዶ/ር ፋሲል በምርምር በተገኙ ውጤቶችና ዕውቀቶች ላይ በመመሥረት በጫሞ ሐይቅ ዙሪያና በሐይቁ ተፋሰስ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ጅምር ሥራዎች እንዲሁም በዚሁ ፕሮግራም አማካኝነት በጫሞ ሐይቅና ተፋሰሱ ላይ የተደረጉ የምርምር ግኝቶችና ጥራት ያላቸው መረጃዎች  ላይ በመመሥረት በሐይቁ ተፋሰስ በሚገኙ 10 ወረዳዎች ላይ ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለመሥራት ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ መሆኑ የዚሁ የትብብር ፕሮግራም ፍሬዎች ናቸው ብለዋል፡፡

የፕሮግራሙን የመጀመሪያ ዙር አፈፃፀምና የ2ውን ዙር የትኩረት መስኮች አስመልክቶ የፕሮግራሙ የሀገር ውስጥና የውጭ አስተባባሪዎች ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስና ፕ/ር ሮውል ሜርሲክስ/Prof Roel Merckx/ ያቀረቡ ሲሆን ፕሮግራሙ በዋናነት በኢትዮጵያ ደቡብ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦችን ፍላጎት ማሟላትና በተመሳሳይ ጊዜ በልማት ሂደት ውስጥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሚጫወተው ሚና ላይ በማተኮር  ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም አንፃር ዩኒቨርሲቲው በማስተማርና ምርምር ያለውን አቅም በማጎልበት በፕሮግራሙ የመማር ዕድል የሚያገኙ ምሩቃን በአካባቢው ከግብርና ምርታማነት፣ ከጤና፣ ከአፈር መከላት፣ ከብዝሃ ሕይወት፣ ከአኗኗር ሁኔታ አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መቅረፍና ዘላቂ ልማትን ማምጣት የሚያስችሉ ምርምሮችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን እንዲሁም በመጀመሪያው ዙር የተገኙ ዕውቀቶችን ማኅበረሰቡን በዘላቂነት እንዲጠቅሙ ወደ መሬት ማውረድ የ2ው ዙር የፕሮግራሙ ትኩረት መሆኑን የገለጹት አስተባባሪዎቹ በዚህኛው ዙርም 14 የዩኒቨርሲቲው መምህራን የ3 ዲግሪ ትምህርት ዕድል እንደሚያገኙም ተናግረዋል፡፡

ለቀጣይ 5 ዓመታት በሥራ ላይ የሚቆየው የፕሮግራሙ 2ኛ ዙር በየዓመቱ 570 ሺህ ዩሮ ዓመታዊ በጀት የተመደበለት ሲሆን የፕሮግራሙ የመጀመሪያው ዙር እንዲሳካ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ላበረከቱ ግለሰቦች የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት