በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2014 ዓ/ም ምሩቃን በብቃት መመዘኛ ፈተና አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል፡፡ የብቃት መመዘኛ ፈተናው በፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጄንሲ በየዓመቱ የሚሰጥ ነው፡፡

ኮሌጁ ካስፈተናቸው የትምህርት ፕሮግራሞች መካከል በፋርማሲ፣ ሚድዋይፋሪ፣ ነርሲንግ፣ አኒስቴዥያና በሜዲካል ራዲዮሎጂ ቴክኖሎጂ የብቃት መመዘኛ ፈተናውን የወሰዱ የወሰዱ የኮሌጁ ምሩቃን ፈተናውን ሙሉ በሙሉ ማለፋቸውን የኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ጠቁመዋል፡፡

የሕክምና ት/ቤት ምሩቃን 91.5 በመቶ ምዘናውን ያለፉ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ታምሩ የተገኘው ውጤት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የሕክምና ት/ቤቶች መካከል በማሳለፍ ምጣኔ የአንደኛነት ደረጃ መገኘቱን አውስተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በማኅበረሰብ ጤና 95.2 ከመቶ እንዲሁም በሜዲካል ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ ፕሮግራም 87 ከመቶ የብቃት ምዘናውን ማላፋቸውን ዶ/ር ታምሩ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ታምሩ ገለጻ የተገኘው ውጤት እንደ ኮሌጅ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ሲሆን በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን አስመርቀው ማስፈተን በቻሉበት በፋርማሲ ትምህርት ፕሮግራም የተመዘገበው ውጤት በእጅጉ አስደሳች መሆኑን ገልጸው ለዚህም ስኬት የመ/ራን ሚና ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡ ለተግባር ልምምድ የተሰጠው ትኩረትና ክትትል፣ በሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅቶችና ክለሳ ላይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር መሥራቱ፣ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለመ/ራን የተሰጡ ሥልጠናዎች ለተመዘገበው አመርቂ ውጤት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዶ/ር ታምሩ ጠቁመዋል፡፡

በምዘና ፈተና አፈጻጸም እንደ ሀገር የተመዘገበው ውጤት  የኮሌጁን ስምና ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ይህም ተማሪዎች በኮሌጁ ተመድበው ሳይሆን ኮሌጁን መርጠው የሚቀላቀሉበት እንዲሆን ያግዛልም ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ለተመዘገበው አመርቂ ውጤት የበኩላቸውን ለተወጡ የኮሌጁ አካዳሚክና አስተዳደር አመራሮች፣ የት/ ክፍል ኃላፊዎች፣ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ የተማሪዎች ኅብረት አመራሮችና አባላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ታምሩ መላውን የኮሌጁንና የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ የደስታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም የተመዘገበውን ውጤት በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል እንዲሁም ከዚህም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ  ሁሉም የትምህርት ፕሮግራሞች አክሪዲት በማስደረግ፣ ለመምህራን የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠትና የትምህርትግብዓቶችን በማሟላት እንዲሁም ለተማሪዎች ሥነ ምግባር መሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ ዶ/ር ታምሩ ተናገረዋል፡፡


                                                                                                                                                                                              የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት