ቀጠናዊ የኢንዱስትሪ ትስስር ፎረሙ ከአከባቢው ኢንዱስትሪዎችና ቴክ/ሙ/ትም/ሥ/ኮሌጆች በዳሰሳ ጥናት የተገኙ ውጤቶች፣ የ2014 ዕቅድ አፈፃፀምና የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ጥቅምት 26/2/2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ተወያይቷል፡፡ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምር/ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደተናገሩት በዚህ ትስስር በዋናነት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሠረታዊ የሳይንስ ዕውቀቶች፣ ምርምሮች፣ ለትግበራ የሚሆኑ የፈጠራ ሃሳቦችና ዲዛይኖች፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን የሚያዘጋጁ ሲሆኑ ኢንዱስትሪዎችና የቴክ/ሙ/ትም/ሥ/ኮሌጆች በበኩላቸው በምርምር ተደግፈው በተጨባጭ የተሠሩ ሃሳባዊ ሥራዎችንና ዲዛይኖችን ቅርፅ ማስያዝ፣ ማሽኖችን መፍጠርና የተፈለጉ ነገሮችን የመሥራት ችሎታውና ዕውቀቱ እንዲሁም ማሽኑ ያላቸው በመሆኑ ከለሎች ዩኒቨርሲቲዎች አንጻር የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተቀራርቦ የመሥራት ሁኔታ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ በተቋማቱ መካከል ያለውን ቅንጅታዊ  ሥራ በማጠናከር በትስስሩ ውጤታማ ለውጥና ዕድገት እንዲታይ ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ የፎረሙ ዓላማ  የኢንዱስትሪውን ብቃትና ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉና የኅብረተሰቡን ችግር ፈቺ የሆኑ ከእሴት ሠንሰለት ጥናት የተለዩና አዋጪነታቸው ተፈትሾ የተረጋገጠላቸውን ቴክኖሎጂዎች በማሸጋገር ሀብት ፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን  እንዲያረጋግጡ ማስቻል ነው፡፡

የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኝና አመራር የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸው ለቴክኖሎጂ ሥራ ሊያግዙ የሚችሉ የሶፍትዌር ሥልጠናዎች መሰጠታቸው፣ ተቋማት በፈቃደኝነት የውይይት አስተናጋጅነት መውሰድና በጥሩ ሁኔታ መሸኘት መቻላቸው፣ ተቋማት ያሉበት ደረጃ በመገምገም የውስጥ አቅማቸውን ለመገንባት ምቹ ሁኔታ መፈጠር፣ የኢንተርፕራይዙን የድጋፍ ጥራት ችግር ለመፍታት የዳሰሳ ጥናት መጀመሩና ውይይት መደረጉ በ2014 ዓ/ም በአፈጻጸም የታዩ ጠንካራ ጎኖች መሆናቸውን የአርባ ምንጭ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ም/ዲን አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል ገልፀዋል፡፡

የፎረሙ ተሳታፊ ተቋማት የፎረሙን ተግባር መዘንጋት፣አዳዲስ ተቋማት በፎረሙ ተገኝተው ልምድ ለመቅሰምና የጋራ ኃላፊነት ለመወጣት ያለው ዝግጁነት ማነስ፣ ፎረሙ በበጀት ተደግፎ አለመመራት፣ የፎረሙ እና የተቋም ተልዕኮ መደበላለቅ ፣ ውጤትን መሠረት ያደረገ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሥርዓት አለመከተል፣ ዕቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ ሰሌዳ ተፈፃሚ የመሆን ውስንነት፣ የልምድ ልውውጥ፣ ጥናት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ማባዛት፣ ማሻሻልና ማሸጋገር ፣ የመረጃ ልውውጥ ክፍተት፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዝቅተኛና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነ መሄድ፣ ውይይት በሚካሄድባቸው ተቋማት ከአደረጃጀት እስከ አሠራር ጉብኝት አለማድረግና ልምድ አለመቅሰም እና በጉድለቶች የጋራ ግንባታ ለማድረግ ያለው መነሳሳት ውስንነት በአፈጻጸም ወቅት የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን አቶ ወርቅነህ አክለዋል፡፡

የ2015 ዕቅድን በተመለከተ አዲስ ወደ ፎረሙ ከተቀላቀሉ  መ/ቤቶች ጋር በመሆን በተካሄደው የጋራ ምክክር የ2015 የጋራ ዕቅድ ረቂቅ የተዘጋጀ ሰሆን የፎረሙ አባል ከሆኑ 5 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት 5 ቴክኖሎጂስቶች መስፈርት አሟልተው ተመልምለው የ2 ዲግሪ ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ መደረጉን አቶ ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡ ቀጣይ  በየዘርፉ መ/ቤቶች በተቀመጠው ግብ መሠረት የፎረሙ ዕቅድ ተግባራት ተፈጻሚ እንደሚሆኑ አቶ ወርቅነህ  አረጋግጠዋል፡፡       

በአ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም ስር የዘርፍ መ/ቤቶች ዓመታዊ የጋራ ዕቅድ የቴክኖሎጂ ኤግዚቨሽንና ፓናል ውይይት ማካሄድ፣ ልምድ ልውውጥ ማድረግና ተሞክሮ ማስፋት፣ የባለድርሻ አካላትና ተጠቃሚ  ተሳትፎ ማሳደግ፣ የማማከር፣ የግብረ መልስና የማሻሻል  አገልግሎት መስጠት፣ የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት፣ የእሴት ሠንሰለት ጥናት እንዲሁም ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ሥራ ማካሄድ የ2015 ዓ/ም ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን በዕቅዱ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት