Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስዊዘርላንድ ሀገር ከሚገኘው ኢት-ዙሪች/ETH-Zurich/ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ገጠርንና ከተማን በንጥረ ነገር ዕሴት ሠንሰለት በሚያስተሳስር “RUNRES/ረንረስ” በተሰኘ ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያዋ ባሉት የገጠር ቀበሌያት ላይ የተለያዩ ተግባራትን ሲሠራ ቆይቶ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በመጠናቀቁ የሥራዎቹን አፈጻጸም እና የፕሮጀክቱን 2 ምዕራፍ ዕቅድና ትግበራ አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ኅዳር 03/2015 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ተቋምነቱ  የተለያዩ ኃላፊነቶች የተሰጡት  መሆኑን ጠቅሰው መማር ማስተማር፣ ምርምርንና ማኅበረሰብ ጉድኝትን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተሻለ ጥራት የማኅበረሰብ ተሳትፎን ባማከለ መንገድ ለመሥራት ትምህርትን በጥራት ከምርምር ጋር አቀናጅቶ መሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ምክትል ፕሬዝደንቱ ገለጻ  የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የአጋር ድርጅቶች ተሳትፎ  ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ በረንረስ ፕሮጀክት አማካኝነት ከስዊዘርላንድ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ሥራዎች ላለፉት 4 ዓመታት ሲሠሩ ቆይቷል፡፡

የ“RUNRES” ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓባይነህ ፈይሶ እንደተናገሩት ተረፈ ምርትን ከማስወገድ በዘለለ መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ግንዛቤን በማሳደግ የገጠር የንጥረ ነገር ዕጥረትንና የከተማ የቆሻሻ አወጋገድን ችግር ለመፍታት ቆሻሻን በማከም ለመሬት ማዳበሪያነት አገልግሎት እንዲውልና ወደ ማሳ በመመለስ ማሳውን መልሶ ለማልማት የሚያስችል ዘላቂ የዕሴት ሠንሰለት መፍጠር መሠረታዊ የፕሮጀክቱ ዓላማ ነው፡፡

አቶ ዓባይነህ  አክለውም ፕሮጀክቱ በውስጡ በርካታ ሥራ አጥ አባላትን መያዙንና ሁለት ማኅበራትን በመደገፍ  አመርቂ ውጤት እንደታየበት የገለጹ ሲሆን ለአብነትም የ“እኛን ነው ማየት ተረፈ ምርት ሽያጭ ማዕከል” የሸማቾችን ተረፈ ምርት፣ የማዘጋጃ ቤታዊና የመፀዳጃ ቤት ቆሻሻን እንዲሁም የገበያ ተረፈ ምርቶችን  አክሞ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሠራ ሲሆን “አንጆ ኑስ የሙዝ ማቀነባበሪያ ማዕከል” ደግሞ በበኩሉ የሙዝ ምርትን ልጦ  ከመመገብ ባሻገር በዱቄት መልክ በማዘጋጀት ለእናቶች፣ ለሕጻናትና በተለያየ ዕድሜ ክልል ያሉትን መመገብ የሚያስችል ለገንፎ፣ ለሙቅና ለሌላም አገልግሎት የሚውል የሙዝ ዱቄት ማዘጋጀት መቻሉንና የልጣጩን ተረፈ ምርት መልሶ ለለተፈጥሮ ማዳበሪያነት ግብዓትነት በማዋል ለአርሶ አደሩ የተሟላ ንጥረ ነገር እንዲገኝና እንዱ ሌላውን መመገብ የሚችልበትን የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓባይነህ ለማኅበራቱ በጥሬ ገንዘብና ሥራውን አመቺ ሊያደርጉ የሚያስችሉ እንዲሁም ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ ማሽኖችን ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በግዥ በማስመጣት እንዲሠሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሥራዎች በተፈለገው ፍጥነት እንደይሄዱ የተለየዩ ተግዳሮቶች እንዳጋጠማቸው በመጠቆም በቀጣይ ምዕራፍ ችግሮችን በመቅረፍ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተሻለ ሥራ ለመሥራት መታቀዱን አቶ ዓባይነህ ገልጸዋል፡፡

ከስዊዘርላንድ ሀገር ከኢት-ዙሪች ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ የደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶ/ር ቤንጃሚን ዋይልድ/Dr Benjamin Wilde/ እንደገለጹት ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት የተመረተው ምርት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንና መርዛማ ንጥረ ነገሮችና ሙቀቱ የበሽታ መተላለፊያ መንገዶችን ሊከላከል እንደሚችል  በሳይንስ መረጋገጡን በመመስከር ከደቡብ አፍሪካ ጋር ሲወዳደርም የተሸለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ዶ/ር ቤንጃሚን የተገኘው ልምድም ቀጣይነት እንዲኖረው አጠናክረን እንሠራለን ብለዋል፡፡

“የእኛን ነው ማየት ማኅበር” መሥራች መ/ር ቦጋለ ቢታኔ ቆሻሻን ሀብት የማድረግ ሳይንስ መተግበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማኅበሩን መመሥረታቸውን ገልጸው ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት መቀየር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሽንትን ወደ ዱቄት መቀየር እንደሚቻልም መ/ር ቦጋለ ገልጸዋል፡፡ እንደ መ/ር ቦጋለ በራንረስ ፕሮጀክት አማካኝነት ከከተማዋ ቆሻሻን ከሚሰበስቡ ማኅበራት ቆሻሻ በግዥ እንደሚያገኙና ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት ምርት በመቀየር የአከባቢውን ምርት ብራንድ ለማድረግ ማኅበራቸው እየሠራ ነው፡፡ የሚያመርቱትን ማዳበሪያ ደረጃ የሚለኩበት ማሽን አለመኖር ተግዳሮት ቢሆንም በፕሮጀክቱ አማካኝነት የተገኙት የሥራ ማሽኖች ጊዜና ጉልበትን እንደሚቆጥቡ የገለጹት መ/ር ቦጋለ ምርቱን አጠናክሮ መሥራት ከተቻለ ከውጭ የሚገባውን ማዳበሪያ በማስቀረት እንደ ሀገር የዶላር ወጪ ማስቀረት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡

የምግብና መጠጥ እንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ መኩሪያ በበኩላቸው እንደተናገሩት ከሙዝ የተቀነባበሩ ምግቦችንና የሙዝ ዱቄት ዝግጅት ሂደት በአካል በመገኘት ምልከታ በማድረግ ከምግብና መድኃኒት ባለሥልጣንና ከደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ደረጃ መውጣት ተችሏል፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህም እንደ ሀገር ባልተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት የሚመጣውን ሞት ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡ ሙዝ በፖታሲየምና በፋይበር እንዲሁም በብዙ ማዕድናት የበለጸገ በመሆኑ ወደ ጥቅም ማስገባት የሀገራችንን የአመጋገብ ሥርዓት እንደሚያስተካክልም አቶ በቀለ ጠቁመዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት እንደጠቀሱት በተረፈ ምርት ማዳበሪያና በሙዝ ምርት አቅርቦት ዕሴት ሠንሰለት ላይ የተሠሩ ሥራዎች ወቅቱን የሚመጥኑና አርሶ አደሩም መሬቱን በሀገር በቀል ማዳበሪያ በማልማት ምርቱን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዙ አበረታች ሥራዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የአቅርቦት መጠኑን በማስፋት ተደራሽነቱ እንዲሰፋ፣ ማኅበራቱ እየሠሯቸው ያሉት መሰል ሥራዎች እንዲተዋወቁና ጎልተው እንዲወጡ ለዘርፉ ዕድገት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ እንዲሁም መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው የምር/ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስን ጨምሮ ከጋሞ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ግብርና መምሪያ፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲሁም  ከብርብር፣ ከገረሴና ከጨንቻ ዙሪያ ወረዳዎች የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የሁለቱ  ማኅበራት ሥራዎችም  በባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታና ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት