በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አማካኝነት በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገው የተዘጋጁ 10 ንድፈ-ሃሳቦች ቀርበው  ኅዳር  9 እና 12/2015 ዓ/ም ግምገማ ተካሂዶባቸዋል፡፡ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ እንደገለፁት የምርምር ንድፈ ሃሳቦች የሚዘጋጁት   ከማኅበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ችግሮችን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ምርምሮች የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ ይገባል ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ የዕለቱ መርሃ-ግብርም የምርምር ሥራዎቹ ወደ ማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራ የሚቀየሩበት ሁኔታ የተመለከተ ነው ብለዋል፡፡ በምርምር ዘርፍ ለዕውቀት የሚሠሩ እንዲሁም ችግር ፈቺ ምርምሮች ያሉ ሲሆን ችግር ፈቺ ምርምሮችን በመምረጥ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲደርሱ ኮሌጁ እየሠራ መሆኑን ዲኑ ጠቅሰዋል፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስ/ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም የቀረቡት ንድፈ ሃሳቦች ከኬሚስትሪ፣ ከባዮሎጂ፣ ከስፖርትና ከጂኦሎጂ ዘርፎች የቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የቀረቡት ንደፈ ሃሳቦች ምርምርን መሠረት አድርገው የማኅበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ  የተዘጋጁ መሆናቸውን የጠቆሙት አስተባባሪው ፍራፍሬንና አትክልትን ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆይ ለማድረግ የቀረበው ንድፈ ሃሳብ ለአብነት ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

በዕለቱ ከቀረቡት ንድፈ ሃሳቦች መካከል የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ  በሆኑት በመ/ር ማሞ ጢቃሞ ‹‹Green Synthesis of Carbon Dots from Vernonia Maygalina (GRAWA)Leaves and Its Applications from the Development of Latent Fingerprints›› በሚል ርዕስ  ያቀረበው ንድፈ ሃሳብ ወንጀልን ለመከላከልና የፍትሕ ሥርዓትን ለማዘመን ከግራዋ ቅጠል የተዘጋጀ ስውር የጣት አሻራን መጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በመ/ርት ቤቴልሄም አበራ ‹‹Application of Banana Peel Starch-Fish Scale Chitosan Composite Edible Film Extending the Storage Quality of Locally Available Fruit›› በሚል ርዕስ የቀረበው ሌላኛው ንድፈ-ሃሳብም የሙዝ ልጣጭንና የዓሳ ቅርፊትን በመጠቀም የፍራፍሬዎችንና የአትክልቶችን የመቆያ ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ የማኅበረሰቡን የአኗኗር ዘዴን የሚያሻሽልና የሥራ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት