የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስ/ጽ/ቤት እና የዩኒቨርሲቲው ባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን እና ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ባህል፣ ቱሪዝምና ፓርኮች ልማት ቢሮ እንዲሁም ከጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር ‹‹የሙዚየም አደረጃጀት፣ አገልግሎት አሠጣጥና ተደራሽነት›› በሚል መሪ ቃል በደቡብ ክልል ካሉ ዞኖች ለተወጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከኅዳር 5-6/2014 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የመጡት አቶ ደምረው ዳኜ እንደገለጹት  የዳሰሳ ጥናት ግኝትን መሠረት በማድረግ  ሥልጠና መስጠት በሙዚየሞች ላይ የሚስተዋሉ የአቅም ውስንነትንና የግንዛቤ ክፍተትን በመሙላት በሀገራችን ያሉ ሙዚየሞች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻልና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ያግዛል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው ለሙዚየሞች አመቺ የሆነ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመዘርጋት የክልሉ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ  ተገቢውን ትኩረት በመስጠት መነቃቃትንና በጋራ ቅንጅታዊ ሥራዎችን ለማምጣት እንዲሁም የሚሰጡ ገንቢ አስተያየቶችን  በግብዓትነት በመጠቀም የተጠናከረ ሥራ እንዲሠራ ለማስቻል የታለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ ሥልጠናዎችን መስጠት የክልልና የፌደራል ተግባር መሆን እንዳለበት ጠቅሰው ለታችኛው የሥራ ክፍል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት መነቃቃትን እንደሚፈጥርና በቀጣይም ሠልጣኞች ያገኙትን ክሂሎት ወደ ተግባር ቀይረው መሥራት ከቻሉ እና ተቋሙም ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ ከቀጠለ  ለውጥ ለማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለድኅነት ቅነሳ እየተከተለች ካለው አንዱ የኢኮኖሚ መሠረት ቱሪዝም በመሆኑ ሙዚየምን እንዴት ማጠናከርና ማደራጀት እንደሚገባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው ዓላማ እንደነበረ አስታውሰው ሙዚየም ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት ከተቻለ የሀገራችንን ዕድገት ማፋጠን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም በዘርፉ ዩኒቨርሲቲውም ትኩረት አድርጎ እየሠራ ያለ በመሆኑ መሰል ሥልጠናዎችን በመስጠት አቅምን የማጎልበትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸው በቀጣይ በጫሞ ካምፓስ የኢትኖግራፊ፣ በዓባያ ካምፓስ የተፈጥሮ እና በዋናው ግቢ የቴክኖሎጂ ሙዚየሞችን ለመቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሰኢድ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ተቋም ዋነኛ ዓላማው ለአከባቢው ባህልና ቅርስ ሙዚየሞች ትኩረት መስጠት በመሆኑ በምርምር የተጀመሩ የቅርስ ሥራዎችና የተለያዩ ዋሻዎች፣ አርኪዮሎጂካል አካባቢዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ሙዚየም  የኅብረተሰብ ሀብት በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ በጋራ መሥራት  ከተቻለ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ብለዋል፡፡

በዕለቱም 6 ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም መካከል፡- የሙዚየም አስተዳደርና አደረጃጀት መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳብ፣ የቅርስ ስብስብ አስተዳደርና አያያዝ፣ መሠረታዊ የሙዚየም ኤግዚብሽን ዝግጅትና አቀራረብ፣ የሙዚየም ትምህርት አገልግሎት ተደራሽነት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የቅርስ ስነዳ የሙዚየም የጀርባ አጥንት ነው ያሉት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የኤግዚብሽን ዝግጅት ባለሙያ አቶ ደምሰው አስፋው የሙዚየም አስተዳደርና አደረጃጀት መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳብ በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን የሚከማቹ ቅርሶች በግዥም ሆነ በስጦታ ሲገኙ የተሟላ መረጃ ሊኖረውና ታሪካዊ አመጣጡ ሊታወቅ እንዲሁም ዓላማው ከተቋሙና ከሀገሪቱ ሕግ አንጻር  የማይጣረስ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ ቅርሶች የባህል ዕሴቶች መገለጫ እንደ መሆናቸው መጠን አስፈላጊ ጥንቃቄና እንክብካቤ እንዲሁም ጥበቃ ከተደረገላቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ እንደሚሆን  አመላክተዋል፡፡

እንደ አቶ ደምሰው ቅርሶች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ፣ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱትን በመለየት ለጥናትና ምርምር፣ ለባህል ማጎልበቻ፣ ለሀገር ግንባታ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለቱሪዝም ዕድገት፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለመማሪያ መጽሐፍ ስነዳ ማዋል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ቅርሶች የጋራ ሃሳብንና ኅብረ ብሔራዊነትን መግለጫ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የቅርስ ዕሴት ያጡ ቅርሶች የአወጋገድ ሥርዓት የተዘረጋ በመሆኑ ሕጉን መከተል እንደሚገባም አቶ ደምሰው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ አቶ መላኩ መሃሪ እንደ ሀገር መንግሥት ለሙዚየምና ለቱሪዝም ትልቅ ትኩረት የሰጠ ቢሆንም ሙዚየም ላይ እየተሠራ ያለው የተግባቦት ሥራ ደካማ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የማስታወቂያ ሥራዎችን በመሥራትና ኅብረተሰቡን በማንቃት ያለውን አመለካከት ለማሳደግ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ መላኩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ጋዜጦች፣ በሬዲዮ፣ ቴሌቭዥንና ኢንተርኔት በመጠቀም ለሕዝብ ለማስተዋወቅና ተደራሽነትን ማስፋት ላይ ጠንካራ ሥራ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ መሥራቱ ጥሩ መነሳሳትና መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው ብዛት ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ ባህሎችና ቅርሶች ባሉባት ሀገር እንደመኖራችን የሙዚየም ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ አደረጃጀቱ በጥልቀት ከተቃኘና ተደራጅቶ መሥራት ከተቻለ እንዲሁም ተከታታይነት ያላቸው መሰል ሥልጠናዎችን ለባለሙያዎች መስጠትና መደገፍ ከተቻለ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

 የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት