የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከ4ቱ ፋከልቲዎችና ከውሃ ምርምር ማዕከል ለተወጣጡ መምህራን ‹‹Basic Python for Environmental Data Processing›› በሚል ርዕስ ከጥቅምት 29 -ኅዳር 10/2015 ዓ/ም ድረስ የቆየ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ሳይንስ ቋሚ ሳይሆን ሁሌም ተለዋዋጭና ራሱን እያሻሻለ የሚሄድ ለመሆኑ  የፓይተን/Python/ የኮምፒውተር ቋንቋ ፕሮግራም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር አብደላ አክለውም ፓይተን ለተለያዩ አገልግሎቶች ከመዋሉም ባሻገር ጊዜ፣ ገንዘብንና ጉልበትን እንደሚቀንስ ገልጸው ሠልጣኞች የሥልጠናውን ግብዓት በመጠቀም የግላቸውን ዕውቀት ለማሳደግ ብዙ ማንበብ እንዲሁም በግልና በቡድን መለማመድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ም/ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ደመላሽ ወንድምአገኘሁ በበኩላቸው የሥልጠናውን ዓላማ ሲገልጹ እንደተናገሩት ሥልጠናው የ2 እና 3 ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር መረጃዎችን ብዙ ውጣ ውረድ ሳይገጥማቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀላሉ በመሰብሰብ ምርምሮችን መሥራት እንዲችሉ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ የበቁ አሠልጣኞችን ማፍራት ነው ብለዋል፡፡  ከኢንስቲትዩቱ 4ቱ ፋከልቲዎችና ከውሃ ምርምር ማዕከል የተወጣጡ 12 መምህራን ለ10 ቀናት ሥልጠናውን መከታተላቸውን ዶ/ር ደመላሽ አክለዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መ/ር፣ የአየር ጥናት ተመራማሪና አሠልጣኝ አቶ ዮሐንስ ዲሪክ ዲንግማንስ /Mr Johannes Dirk Dingemanse/ በአካባቢ ምኅንድስና ዘርፍ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ለማውረድና የወረዱትን መረጃዎች በመተንተን ለምርምርና ለመማር ማስተማር አገልግሎት መጠቀም እንዲቻል የሚረዳ የኮምፒውተር ቋንቋ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡ አክለውም  ፓይተን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ስለሚሰጥ ሌሎች የሥራ ክፍሎችም ሥልጠናውን እንዲወስዱና ሥልጠናውን የወሰዱት መምህራን ደግሞ ሌሎችን እንዲያሠለጥኑ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ሥልጠናው በተለይ በውሃ ዘርፍ ለሚሠሩ ምርምሮች ትልቅ ግብዓት ይሆናል ያሉት ሠልጣኝ መ/ር አቤኔዘር ሉቃስ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ለሁሉም መምህራን ቢዳረስ ከመማር ማስተማር ባለፈ በውሃው ምኅንድስናና ምርምር ዘርፍ ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችልና አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይም ለሠልጣኝ መ/ራን የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት