ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል የምርምር ንድፈ ሃሳቦች ግምገማ ኅዳር 12/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኩዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በማዕከሉ የሚከናወኑ ምርምሮችና እንዲፀድቁ የሚቀርቡ የምርምር ንድፈ ሃሳቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ምርምር ማዕከል ምርምሮችን ከማከናወን ባሻገር የጥናት ውጤቶቹን በታዋቂ የምርምር ጆርናሎች ላይ ማሳተም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ታምሩ በዩኒቨርሲቲው የተመቻቸውን የማበረታቻ ሥርዓት በመጠቀም በዘርፉ ያለውን አፈፃፀም ከፍ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ረ/ፕ ፀጋዬ ዮሐንስ በማዕከሉ ከ50 በላይ መደበኛና 4 ሜጋ የምርምር ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት 26 የምርምር ንድፈ ሃሳቦች ለማዕከሉ የቀረቡ ሲሆን በማዕከሉ ተመራማሪዎች በተደረገ የመጀመሪያ ዙር ግምገማ ከማዕከሉ የሥራ ዓለማ ጋር የሚስማሙ 16 ንድፈ ሃሳቦች ተመርጠው ለግምገማ መቅረባቸውን ረ/ፕ ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ጉልህ ሚና የሚጫወቱ እንዲሁም በሂደት ወደ ማኅበረሰብ ወርደው የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ የተሻሉ ንድፈ ሃሳቦችን መለየት የግምገማው ዓላማ ሲሆን ከቀረቡ ንድፈ ሃሳቦች መካከልም 12ቱ በ2015 በጀት ዓመት ወደ ትግበራ ይገባሉ፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት