በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስ/ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን ገቢዎች ባለሥልጣንና ከካምባ ከተማ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በካምባ ከተማ ለሚገኙ ነጋዴዎችና ግብር ሰብሳቢ ባለሙያዎች በሂሳብ መዝገብ አያያዝ ዙሪያ ከኅዳር 8-9/2015 ዓ/ም ድረስ የ2 ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ የታክስ ትምህርትና ኮሚዩኒኬሽን ቡድን መሪ ወ/ሮ መሳይ ተስፋዬ  ሥልጠናው በዋናነት ለደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዩች እንዲሁም በፈቃደኝነት የሂሳብ መዝገብ ለሚይዙ ደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የተዘጋጀ ነው፡፡ ግብር ከፋዮች በፈቃደኝነት የሚጠበቅባቸውን ግብር እንዲከፍሉና ወጪና ገቢያቸውን በትክክል መለየት እንዲችሉ ማስቻል እንዲሁም ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ደረሰኝ በአግባቡ መጠቀም እንዲችልና የሚፈለግበትን ግብር በወቅቱ እንዲከፍል ማድረግ የሥልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑንም ቡድን መሪዋ ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ መሳይ አክለውም መሰል ሥልጠናዎች ግምታዊ የሆኑ አሠራሮችን በማስቀረት የመስኩን ሥራ የተቀላጠፈና ውጤታማ እንዲሆን ይረዳልም ብለዋል፡፡

የካምባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማውሬ በበኩላቸው ለአንድ ሀገር ዕድገት ግብር መክፈል ወሳኝና የዜግነት ግዴታ ጭምር መሆኑን ጠቅሰው መሰል ሥልጠናዎች በነጋዴውና በግብር ሰብሳቢው መካከል የሚፈጠሩትን ቅራኔዎች ለማስወገድ የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስ/ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ርት አስቴር ሰይፉ   ሥልጠናው በግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ዘንድ ያለውን የአሠራር ክፍተት የሚቀርፍና ሳይንሳዊ አሠራሮች ተግባር ላይ እንዲውሉ በማድረግ ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ ድርሻ የሚያበረክት ነው ብለዋል፡፡ ኮሌጁ በቀጣይ ጊዜያት በመስኩ የሚስተዋሉ የሳይንሳዊ ዕውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት አቅዶ እየሠራ መሆኑንም አስተባባሪዋ አውስተዋል፡፡

የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ጣሂር ደስታ ሥልጠናው  በሂሳብ መዝገብ አያያዝ ምንነትና ግብር ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥና ዕድገት ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ግንዛቤ የተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም መሠል ሥልጠናዎች በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክረው መቀጠል ቢችሉና  በመስኩ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች የድጋፍና የክትትል ሥራ ቢጠናከር በዘርፉ አሠራር ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ሥልጠናው በሂሳብ መዝገብ አያያዝ፣ በደረሰኝ አጠቃቀም፣ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ የታክስ አስተዳደርና አዋጅ ቁጥር 166/2009 እና የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 165/2009 መመሪያዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ 

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በዘርፉ አሠራር ላይ ያለባቸውን የዕውቀት ክፍተት የሞላ በመሆኑ በቀጣይም አዳዲስ የሚመጡ አሠራሮችን በዚህ መልክ ተደራሽ የማድረግና የማሳወቅ ሥራ ዩኒቨርሲቲው አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት