Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክቶሬት የ2015 ዓ/ም የቴክኖሎጂ ሽግግር ንድፈ ሃሳቦችን መምህራን፣ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት ኅዳር 13/2015 ዓ/ም አስገምግሟል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው ዩኒቨርሲቲ- ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በተለያዩ ዘርፎች የአርሶ አደሩንና የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን  ገምግሞ ውጤታማ የሆኑትን  መለየትና ለማኅበረሰቡ  ማሸጋገር የዳይሬክቶሬታቸው ዋና ተግባር መሆኑን ጠቅሰው የንድፈ ሃሳብ ግምገማው ነሐሴ 2014 ዓ/ም በወጣው የንድፈ ሃሳብ  ወረቀት ጥሪ መሠረት  የቀረቡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ንድፈ ሃሳቦችን ለመገምገምና ውጤታማ የሆኑትን ለይቶ በ2015 ዓ/ም ወደ ትግበራ ለማስገባት መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱም “Banana Machine Development  and Testing at Community Level”፣ “Introduction and Scaling up of Climate Smart Improved Potato Technologies in  Potential Potato Producing Areas of Ethiopia”፣ “Constructing and Evaluating Groundnut Ethiopian Cardamom Seed Sheller Machine and Energy Free Water Delivery System” እና “Small-Scale Innovative Mechanical Press Extraction of Neem (Azadiracta lndica) Seed Oil for Multi-Benefits in the Manufacturing of Soaps” የሚሉና  ሌሎችም በአጠቃላይ 18 ንድፈ ሃሳቦች ተገምግመዋል፡፡

የቀረቡት የቴክኖሎጂ ሽግግር ንድፈ ሃሳቦች በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሩ ዘሩን በቀላሉ መሰብሰብ እንዲችል የሚረዱ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ለገበያ ቀርበው ቢዝነስ መፍጠር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂ ውጤቶችና ሌሎች የማኅበረሰቡን  ችግሮች ለመፍታት በሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት