በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል አዘጋጅነት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ9 ጊዜ የሚከበረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ሳምንት በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ኅዳር 16/2015 ዓ/ም በፓናል ውይይትና የቢዝነስ ውድድር በማካሄድ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የፈጠራ ሥራ ከፍ ያለ የአዕምሮ እና የአካል የተቀናጀ እንቅስቃሴን የሚጠይቅ ተግባር ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ትምህርት ፈጠራዊ፣ ሃሳባዊና ተጠየቃዊ እንዲሁም ችግር ፈቺ የሆኑ የአዕምሮ ክሂሎቶችን ከማሳደጉም ባሻገር ያለውን አቅም በመጠቀም ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን፣ ግንዛቤዎችንና ክሂሎቶችን አደራጅቶ ችግር ፈቺ የሆነ የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ከፍ ያለ ሚና ያለው ሲሆን ይህም ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ዝንባሌና ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ዳምጠው አክለውም በዩኒቨርሲቲው ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ የተማሪዎች የፈጠራ ሥራ ውድድር ሲከናወን የቆየ ሲሆን በተለይ በ2013 ዓ/ም ማጠናቀቂያ ላይ ከተወዳደሩ ተማሪዎች መካከል በሀገር ደረጃ ተወዳድረው ከፍተኛ ሽልማት ያገኙ እንደነበሩ ጠቁመው ተማሪዎችና ወጣቶች በፈጠራ ሥራ ላይ የሚያደርጉትን ጥረት ለማበረታታት እንዲሁም ተማሪዎች ከመ/ራን ጋር እየተመካከሩ ለምረቃ ማሟያ የሚሠሯቸውን ፕሮጀክቶችም ይሁን ሌሎች በትምህርት ቆይታ ሂደት ውስጥ ሆነው የሚሠሯቸውን የፈጠራ ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እንደሚደግፍ ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት የዓለም የሥራ ፈጠራ ሳምንት በዓለም ትልቁ የሥራ ፈጠራ ፌስቲቫል ሲሆን ከ180 በላይ በሆኑ የዓለም ሀገራት ከኅዳር 21 - 27 የሚከበር ሲሆን ፋይዳውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም ሀገርና ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎች የሚያደርጉትን ጥረት ለመዘከር በመስኩ ያሉትን ተግዳሮቶች በመቋቋም ለሚያመጡት አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ዕውቅና በመስጠት ማክበርና አዳዲስ የሥራ ዕድል ፈጣሪዎችን ማበረታታትና ማብቃት ነው ብለዋል፡፡

ተ/ፕ በኃይሉ አክለውም በሳምንቱ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የንግድ ሥራ ባለቤቶችና ኩባንያዎች ለግለሰቦች፣ ለሥራ ፈጣሪዎች፣ ለአነስተኛ የንግድ ሥራ ባለቤቶችና ከፍተኛ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎችም ጭምር ሃሳባቸውን እንዲለኩ፣ እንዲያሳውቁ፣ እንዲያፈልቁ እና ነጻ የሆነ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከትላልቅ ውድድሮች እስከ አውታረ መረብ ስብሰባዎች ተሳታፊዎችን በማቀራረብ ተባባሪዎች፣ አማካሪዎችና ባለሀብቶችን በማገናኘት ታላቅ ሥራ የሚፈጥር ትልቅ ዕድልን የሚያስተዋውቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

ለፓናል ውይይቱ መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦችን ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር  ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቢዝነስ ሃሳብ ፈጣሪዎች ጅማሬ ላይ የሚያጋጥማቸው በርካታ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጉዳዮችን የሚያዩበት፣ ከፋይናንስ፣ ከተሳካላቸው ሥራ ፈጣሪዎች፣ ከትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ጋር ትስስር የሚፈጥሩበት ነው፡፡ እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ሳምንት አከባበሩ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለይም ተማሪዎች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች ለሥራ ፈጠራዎች ምቹ የሆነ ስነ-ምኅዳርን በመፍጠር ሂደት እንደ ዩኒቨርሲቲ ልንጫወተው የሚገባንን ሚና ለይተን በማወቅ በቀጣይ ለመሥራት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡  

የቢዝነስ ሃሳብ ይዘው ለሚመጡ ተማሪዎች ግንዛቤ መፍጠርና ለሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ምኅዳር መፍጠር ከዩኒቨርሲቲው ይጠበቃል ያሉት ዶ/ር ወንደሰን ዩኒቨርሲቲውን መሠረት የደረገ የሥራ ፈጠራ ስነ-ምኀዳር ሲባል ተቋሙ ለሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት፣ ኃላፊነት ወስዶ የሚመራበት፣ የውስጥና የውጪውን ማኅበረሰብ በዕውቀት፣ በሳይንስ፣ በምርምር የታገዘ ድጋፍ የሚያደርግበት ሲሆን ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበት ሚና በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የዓለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችን፣ ዕውቀቶችን እየለየ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት ባሻገር የራሳቸውን የቢዝነስ ሃሳብ የሚጀምሩ ይሆኑ ዘንድ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ዶ/ር ወንድወሰን በተጨማሪም የምርምርና የቴክኖሎጂ ሥራዎች ገበያ ተኮር ይሆኑ ዘንድ ከተፈጠሩ በኋላ ተገቢው ግምገማ ተካሂዶባቸው ለሥራ ፈጣሪዎች ቴክኖሎጂን የሚያሸጋግር ሆኖ ሃሳቡን ወደ ቢዝነስ የመቀየር ኃላፊነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የሥራ አጥነት ችግር መላ ዓለምን የሚፈታተንበት ጊዜ ላይ እንደመሆናችን መጠን ተወዳዳሪ፣ የሚፈጥር፣ የራሱን ሥራ የሚጀምር፣ ታግሎ የማይወድቅ፣ ድል አድርጎ ውጤታማ የሚሆን ትውልድ ማፍራት ይጠይቃል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም አዲስ የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸው ተማሪዎች የቢዝነስ ሃሳብ ዕቅዶቻቸውን አቅርበው በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎች ከተገመገመ በኋላ ከ1 እስከ 5 ለወጡ ተወዳዳሪዎች በየደረጃቸው የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በፕሮግራሙ የተለያዩ ሃሳብ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የካውንስል አባላት፣ የመ/ራንና የተማሪዎች ተወካዮች፣ አዲስ የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸው ተማሪዎች እንዲሁም ከጋሞ ዞን ከተለያዩ ተቋማትና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ  ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት