Print

የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲዊዘርላንድ ሀገር ከሚገኝ "Eawag" ከተሰኘ የምርምር ማዕከል ጋር በመሆን ለውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህራን በሳኒቴሽን ዘዴና ቴክኖሎጂ ምርጫ /Sanitation System and Technology Choices/ በሚል ርዕስ ከኅዳር 15-16/2014 ዓ.ም ድረስ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በኢንስቲትዩቱ የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ ዲን አቶ ዘነበ አመለ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በሳኒቴሽን ዙሪያ መሠረታዊ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው ሥልጠናውም እነዚህን ችግሮች መሠረት በማድረግ ሲውዘርላንድ ሀገር ከሚገኘው "Eawag" ከተሰኘ የምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሥልጠናው መምህራን በዘርፉ ላይ በቂ ዕውቀት አግኝተው ለተማሪዎቻቸው የተሻለ ዕውቀት እንዲያስጨብጡና ለሚያከናውኗቸው የምርምር ሥራዎች የሚረዱ ግንዛቤዎችንና አዳዲስ አሠራሮችን እንዲያገኙ የሚረዳ ነውም ብለዋል፡፡ በማኅበረሰባችን ውስጥ በሳኒቴሽን ዘርፍ ከውሃ አቅርቦት አንፃር የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚያስችሉ፣ ከቆሻሻ አወጋገድና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለመዋል በሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያም ግንዛቤ የተፈጠረበት ሥልጠና መሆኑንም ዲኑ አክለዋል፡፡

የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና የሥልጠናው አስተባባሪ ዶ/ር ክንፈ ካሳ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የሲዊዘርላንዱ  "Eawag" የምርምር ማዕከል ጋር በሳኒቴሽን ዘርፍ በትብብር እየሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡  ሥልጠናው ከዚሁ ምርምር ማዕከል በመጡ አሠልጣኝ የተሰጠ ሲሆን የፍሳሽ ቆሻሻን ለማከም በሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ላይ እንዲሁም የትኞቹ ቴክኖሎጂዎች ለየትኛው መሬት እንደሚሆኑና ይህንንም ለዲዛይን ሥራ በምን መልኩ መጠቀም ይቻላል በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮችና ሌሎች ተያያዥ የዘርፉ ሥራዎች ዙሪያ ግንዛቤና የቴክኖሎጂ ትውውቅ የተፈጠረበት መሆኑን አውስተዋል፡፡

ከሲዊዘርላንድ "Eawag" የምርምር ማዕከል የመጡት አሠልጣኝ ዶ/ር ሰፉለር ዶሮቲ /Sphuler Dorothee/ በበኩላቸው ተቋማቸው በዘርፉ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ተቋማቸው በትብብር አብረውት ለሚሠሩ ዩኒቨርሲቲዎች "Sanitation System and Technology Choices" በሚል ርዕስ ሥልጠና እየሠጠ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡  የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከተቋማቸው ጋር በትብብር ከሚሠሩ ተቋማት አንዱ በመሆኑ ሥልጠናው ለኢንስቲትዩቱ  የውሃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህራን እና የ2ና 3 ዲግሪ ተማሪዎች ተሰጥቷልም ብለዋል፡፡  ሥልጠናው በሳኒቴሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዘዴና ምርጫ ላይ ለፋከልቲው መምህራን፣  ተመራማሪዎችና ተማሪዎች አቅም ለማሳደግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑንም አሠልጣኟ ተናግረዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የፋከልቲው መ/ር አብኔዘር ሉቃስ በሰጡት አስተያየት  ሥልጠናው የመምህራንን አቅም ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑን ተናግረው ይህም ለቀጣይ ሥራዎች አጋዥ የሆኑ አዳዲስ ዕውቀቶችን የገበዩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት