የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ፆታዊ ጥቃትንና ትንኮሳን አስመልክቶ ለሳውላ ካምፓስ ተማሪዎች ታኅሣሥ 8/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በፆታና ሥርዓተ ፆታ መካከል ያለውን ልዩነት አስመልክቶ ሥልጠና የሰጡት የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ እንደገለጹት ፆታ በተፈጥሮ የሚገኝ ሲሆን ሥርዓተ-ፆታ ደግሞ በአንድ በተወሰነ ማኅበረሰብ ዘንድ ለወንድም ሆነ ሴት የሚሰጥ ሚና፣ ባህርይ እንዲሁም የሥልጣን አስተዋጽዖ ነው ብለዋል፡፡  

አቶ ታደለ አክለውም ሴቶች ለችግር ከሚያጋልጧቸው ነገሮች ራሳቸውን በማራቅና እርስ በራስ በመደጋገፍ የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩና የሀገራቸውን፣ አካባቢያቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ስም በመልካም ተግባር እንዲያስጠሩ መክረዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ በሰጡት ሥልጠና ፆታዊ ጥቃት ጾታን ብቻ መሠረት በማድረግ በግለሰቦች ስነልቦናዊና አካላዊ ጤንነት እና ዕድገት እንዲሁም ማንነት ላይ አሉታዊ ጉዳት የሚያደርሱ ማንኛውንም ተግባራት መፈጸም ሲሆን ይህም ኃይልን በመጠቀም ያለግለሰቦች ስምምነት የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል፡፡

አቶ ዛፉ አክለውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ፈርጀ ብዙ  ፆታዊ ጥቃቶች የሚፈጸሙ ሲሆን  ከነዚህም መካከል የቃል እና የጽሑፍ ትንኮሳዎች፣ ወሲባዊ ትንኮሳዎች እንዲሁም አካላዊና  ስነልቦናዊ ጥቃቶች ይገኙበታል፡፡ በመሆኑም ሴት ተማሪዎች መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ጓደኞች በመራቅ ትምህርታቸው ላይ ማተኮር፣ ወሲባዊ ትንኮሳ ሲደርስባቸው ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ተገቢ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ፣ በዩኒቨርሲቲው የሚሰጡ የምክር አገልግሎቶችን የመጠቀም ልምድ ማዳበር፣ በራስ የመተማመን እና ለራሳችን የምንሰጠውን ግምት ማሳደግ፣ የጭፈራ፣ ጫትና ሺሻ ቤቶች ለጾታዊ ጥቃት እንደሚያጋልጡ በማወቅ መጠንቀቅ እንደሚገባ አቶ ዛፉ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም እነዚህ ጥቃቶች ሕገ መንግሥቱን እና የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲውን የሚቃረኑ እንዲሁም ሀገሪቱ ከድኅነት ለመውጣት ለምታደርገው ጥረት እንቅፋት መሆናቸውን ተገንዝበን በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ እና የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

በመጨረሻም እንደሳውላ ካምፓስ ፆታዊ ትንኮሳን ለመከላከል ሊሻሻሉና ማስተካከያ ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች  ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡  

                                                                                                                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት