የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴምክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ኃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ከታኅሣሥ 9-11/2015 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምልከታ አድርገዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ኃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባላት በሰጡት የምልከታ ግብረ-መልስ እንዳመላከቱት ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርሲቲው በነበረው ቆይታ ተቋሙ በመማር ማስተማር፣ ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት በኩል ያሉ የሥራ እንቅስቃሴዎችን ከቁልፍ የተግባር አመላካቾች አንፃር መመልከቱን ጠቁመዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በቆይታው ከዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት፣ ከግዥ፣ ከፋይናንስና ኦዲት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው መምህራን ጋር ውይይት በማድረግ መረጃ መሰብሰባቸውንም አመላክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከምሥረታው አንስቶ በተለይ በውሃው ዘርፍ ብቃት ያላቸው ምሁራንን ማፍራት ማስቀጠሉ፣ የምርምር ዩኒቨርሲቲን የሚመጥን አደረጃጀት ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት፣ ካለው ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሠላማዊ መማር ማስተማርን ማስቀጠል መቻል፣ በእንሰት ዙሪያ የሚደረጉ ምርምሮችና የፈጠራ ሥራዎች፣ በታዳሽ ኃይል አቅርቦት አንፃር የተሠሩ ሥራዎችና ለሴት ተማሪዎች የሚደረጉ ድጋፎች፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎችና ሠርቶ ማሳያዎች ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ የተመለከታቸው ተግባራት መሆናቸውን ም/ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡ በዋናነት በሳውላ ካምፓስ የሚስተዋለው የመማሪያ ክፍል፣ የቤተ-ሙከራ፣ የግብዓት ዕጥረትና ግዥዎች በወቅቱ አለመፈጸም፣ የመምህራን ክፍያዎች መዘግየትና በኦዲት ግኝቶች ላይ የተሟሉ የማስተካከያ እርምጃዎች አለመወሰድ ቋሚ ኮሚቴው ማስተካከያ እንዲደረግባቸው የለያቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ዶ/ር ከይረዲን ጠቁመዋል፡፡

ተጀምረው የቆሙ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ሥራ ማስጀመርና ማጠናቀቅ፣ የቤተ-ሙከራ ግብዓቶችን ማሟላት፣ የውስጥ ገቢን ማሳደግ፣ የውስጥ ኦዲትን በሰው ኃይልና በአሠራር ማጠናከር፣ በዩኒቨርሲቲው አቅም በሚመለሱ የመምህራን ጥያቄዎች ላይ ወቅታዊ ምላሽ መስጠት፣ ራስ አገዝ መሆንን ለማረጋገጥ አሠራሮችን ማሻሻልና ዕቅዶችን መከለስ፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚደረጉ የትብብር ሥራዎችን ማጠናከርና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ዶ/ር ከይረዲን አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በቋሚ ኮሜቴው አባላት የተሰጡ አስተያየቶችና ጥቆማዎች ለዩኒቨርሲቲው ቀጣይ የትኩረት ሥራዎች አጋዥ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን በመጠቀም ለማስተካከል ዕቅድ ይዞ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡  ከሳውላ ካምፓስ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን መቅረፍ በተመለከተ ዩኒቨርሲቲው ባለው አቅም ሁሉ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ግንባታዎችን ማካሄድ በበቂ ሁኔታ ባላመፈቀዱ በካምፓሱ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት