Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ማእከል ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31 በሀገራችን ለ30ጊዜ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን ከ6ቱም ካምፓስ ከመጡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጋር ታኅሣሥ 9/2015 ዓ/ም ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ማእከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካፒታ ዋልጬ እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ሙሉ የምናደርገውና ውጤታማ ሥራ የምንሠራው አካል ጉዳተኞችን ማካተት ስንችል ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች አቅማቸውን አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ ሁሉም የማኅበረሰብ  ክፍል የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ ቀኑን ስናከብር በዩኒቨርሲቲያችን ያሉ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ክፍሎች ለመስተናገድ ሲመጡ ፈጣን ምላሽ በመስጠት በመማር ማስተማርና ምርምር ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ እንዳለብን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

በዳይሬክቶሬቱ የልዩ ፍላጎት ባለሙያ ወ/ሮ ዳግማዊት አባይነህ የተባባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዛሬ 31 ዓመት ኅዳር 24 ቀን የአካል ጉዳተኞች ቀን ሆኖ እንዲከበር ሲወስን አካል ጉዳተኞች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች መብታቸውን የሚጠይቁበት እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲያችን ለአካል ጉዳተኞች እንደየፍላጎታቸው ድጋፍ ለማድረግ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች ለተወጣጡ አገልግሎት ሰጪዎች የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ባለሙያዋ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ተወካይ ተማሪ አገዘ አስናቀ የዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ሥራ ክፍሎች አገልግሎት ፈልገው ለሚመጡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በቀናነት ማስተናገድና መደገፍ እንደሚገባቸው አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በፕሮግራሙ የተማሪዎች አገልግሎት ማእከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካፒታ ዋልጬ፣ የተማሪዎች ኅብረት ፓርላማ ፕሬዝደንት ተማሪ ደስያለው ቆለጭ፣ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ አገዜ አስናቀ፣ የሰላም ፎረም ፕሬዝደንት ተማሪ መብራቱ ተስፋዬ፣ የተማሪ ኅብረት ፓርላማ አመራሮች፣ የሁሉም ካምፓሶች የልዩ ፍላጎት ባለሙያዎችና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡   

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት