Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአምስቱ ካምፓስ ተማሪዎች ፓርላማ አባላት ጋር የመውጫ ፈተና አሰጣጥ መመሪያ አተገባበርን በተመለከተ ታኅሣሥ 6/2015 ዓ/ም ገለጻና ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት የመውጫ ፈተና እንደ ሀገር ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ በዓመት ሁለት ጊዜ ለተመራቂ ተማሪዎች ይሰጣል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ምሩቃን ብቃት ያላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ፣ በሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ገበያ ላይ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ የሆኑ ምሩቃንን ለማፍራትና ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ለመዘርጋት የመውጫ ፈተና አስፈላጊ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ የፈተናው ዋና ዓላማ ዕጩ ምሩቃን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቆይታቸው በሥርዓተ ትምህርቱ በተቀመጠው መሠረት ዕውቀትና ክሂሎታቸውን መመዘን ሲሆን አንድ ተማሪ ፈተናውን ባያልፍ ላልተገደበ ጊዜ መፈተን እንደሚችል መመሪያው ይገልጻል ብለዋል፡፡ ለትምህርት ጥራትና ለፈተናው ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ም/ፕሬዝንቱ አሳስበዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ትግበራና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ በበኩላቸው ትምህርት ሚኒስቴር በዕቅድ ከያዛቸው የለውጥ ሥራዎች አንዱ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ሲሆን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚረዱ መንገዶች አንዱ የመውጫ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ሠረቀብርሃን የፈተናው ምንነት፣ አተገባበሩና ለተማሪው የሚሰጥበት ሂደት ላይ በየደረጃው የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ይሰጣል ብለዋል፡፡

የመውጫ ፈተናውን በተመለከተ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ፣ ለፈተና የመዘጋጃ ጊዜ፣ እንደ ሀገር በየትምህርት ክፍሉ የሚሰጡ ፈተናዎች ተመሳሳይነት፣ የ ‹‹Core competence›› ምንነት እና የቤተ ሙከራ ኮርስ ጥያቄዎች አዘገጃጀት ላይ ተሳታፊዎች በሰፊው ተወያይተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት