Print

የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ለሚገኙ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ከታኅሣሥ 13-14/2015 ዓ/ም የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው የሕዝብ ግንኙነት መሠረታዊያንና አተገባበር፣ የዜና አጻጻፍ መሠረታዊያን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና የጥሩ ዘጋቢ መለያ ባህሪያት በሚሉ ይዘቶች ዙሪ ያተኮረ ነው፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሹሬ ደረጃውን የጠበቀ መረጃ በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ለመፍጠር ሥልጠናው መሰጠቱን ጠቅሰው ባለሙያዎች ከሥልጠናው ያገኙትን ክሂሎት ተጠቅመው በተሻለ ሁኔታ መረጃ ለማኅበረሰቡ በፍጥነት ማድረስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ መሐመድ ወቅቱ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ሐሰተኛ መረጃ ከመሰራጨቱ በፊትም ሆነ በኋላ ለማኅበረሰቡ በአፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ አጭር፣ ግልጽና ተዓማኒ መረጃዎችን ከዲጂታል ሚዲያ በተጨማሪ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ተጠቅሞ ማድረስ ይገባል፡፡

የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ኤደን ንጉሤ ሠልጣኞች ለማኅበረሰቡ ጥራቱን የጠበቀ፣ የተቀናጀና ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸው ሥልጠናው ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ አቅም የሚፈጥርላቸው ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሥልጣኔ ሊመጣ የሚችለው ጥሩ ተግባቦት ሲኖር ነው›› ያሉት በዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ት/ክፍል መምህርትና አሠልጣኝ ወ/ሮ ታሪኳ እሸቱ በልምድ ከመሥራት ይልቅ በሥልጠና ተደግፈው በሳይንሳዊ መንገድ ቢሠሩ የተግባቦት ሂደቱን ማሳለጥ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ባለሙያዎች ተከታታይነት ባላቸው ሥልጠናዎች ክሂሎታቸውን ሲያዳብሩ ትክክለኛና ሳቢ ዜና ማቅረብ ይችላሉ ያሉት አሠልጣኟ በሥራ ላይ የሚፈጠሩ ግድፈቶችን ከመቅረፍ ባሻገር መንግሥት እያደረገ  ባለው የልማት እንቅስቃሴ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ 

በእንግሊዝኛ ት/ክፍል የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርና አሠልጣኝ አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ በበኩላቸው በሥልጠናው እንደ ባለሙያ ሕዝብና መንግሥት ጋር ያለውን የመረጃ ፍሰት እንዴት ማቀናጀት እንደሚገባ ከጽንሰ ሃሳብ እስከ ተግባር ሙከራዎች ለማየት  እንደቻሉ ጠቅሰዋል፡፡ ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን መተግበርና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ራሳቸውም ሆነ ማኅበረሰቡ በተሻለ ሁኔታ የሚጠቀምበትን መንገድ መፍጠር ከቻሉ ለሥራው መሻሻል አበርክቶው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የዲታ ወረዳ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ባለሙያና ሠልጣኝ አቶ ዮሃንስ ባይሳ በዜናና ዘገባ አጻጻፍ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውንና የዕይታ አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ሥልጠናው ያገዛቸው መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ሌላኛው ሠልጣኝ የገረሴ ዙሪያ ወረዳ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ እንዳለ ኢያሱ በበኩላቸው ሥልጠናው ሰፊ ጊዜ ተይዞለትና ሌሎች ፈጻሚዎችንም በማካተት የሚሰጥበት ዕድል ቢመቻች በብቃት ችግር የሚመጡ ብዥታዎችን ለማጥራት እንዲሁም  ጥሩ የመረጃ አቀራረብ እንዲኖር የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥልጠናው ከጋሞ ዞን፣ ወረዳዎችና ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ 60 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

                                                                                                                                   የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት