Print

የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ከጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ ጋር በመተባበር ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለተወጣጡ መርማሪ ፖሊሶች በፎረሲንክ ወንጀል ምርመራ ዘዴ እና የፎረንሲክ ማስረጃ ዝግጅት ዙሪያ ከታኅሣሥ 12-14/ 2015 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ እንደገለጹት ፖሊሶች ያላቸውን ልምድ ከጽንሰ ሃሳብ ዕውቀት ጋር በማጣመር በጋራ ለመሥራትና የወንጀል ምርመራ ሂደት ጥራትን ለማስጠበቅ ሥልጠናው ጉልህ ሚና አለው፡፡ ወንጀል የረቀቀና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም በሳይንሳዊ መንገድ ተጠቅሞ ሕግን ለማስጠበቅ የዘርፉ ባለሙያዎች በዕውቀትና በክሂሎት የተገነቡ መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዲኑ ወንጀልን ለመከላከልና ፍትሕን ለማስፈን ዩኒቨርሲቲው በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማ/ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ገ/ማርያም በበኩላቸው ሥልጠናው ለ2ኛ ጊዜ የተሰጠ መሆኑን አስታውሰው ሥልጠናው በጽንሰ ሃሳብና በተግባር ተደግፎ መሰጠቱ በፖሊስ ምርመራ መዝገብ የፎረንሲክ ማስረጃዎች ላይ የሚስተዋሉ የጥራት፣ የዕውቀትና የክሂሎት ክፍተቶችን ለመቅረፍ ይረዳል ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ የፎረንሲክ ዋና አስተባባሪ ም/ኢንስፔክተር ስንዱ አየለ የፎረንሲክ ምርመራ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ቢሆንም በኢትዮጵያ የፎረንሲክ ሥልጠና በውስን ቦታዎች ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ጎልቶ የማይታወቅና ቦታ ያልተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው የዕውቀት ክፍተቶችን በማጥበብ በወንጀል ምርመራ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ም/ኢንስፔክተር ስንዱ ገልጸዋል፡፡

የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ት/ክፍል መምህር አቶ ማሞ ጢቃሞ  የፎረንሲክ ሰነድ ምርመራ፣ ድብቅ የጣት አሻራ፣ የጫማ ዳና፣ ቃጠሎና ፍንዳታን በተመከለተ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ እንደ አሠልጣኙ የእጅ ጽሑፍ፣ ፊርማ፣ የማኅተምና የቲከር ኅትመቶች እንዲሁም የቃጠሎና ፍንዳታን የተመለከቱ ሰነዶች በፎረንሲክ ሰነድ ምርመራ ላብራቶሪ የሚመረመሩ ናቸው፡፡

ሌላኛዋ የት/ክፍሉ መምህርትወ/ሮ አሰለፈች አየለ በበኩላቸው የወንጀል ትዕይንት ምርመራ፣ የወንጀል ትዕይንት ሂደት የማጣቀሻ ናሙናዎችን ማግኘት፣ የጥበቃ ሰንሰለት በመሳሰሉት ላይ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ራሳቸውን በዕውቀትና በክሂሎት እንዲያጎለብቱ፣ ከልምድ ሥራ እንዲወጡና ከቀድሞው የአሠራር ሂደት በተለየ ሁኔታ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በሥልጠናው ላይ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለሠልጣኞችም የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

                                                                                                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት