የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞና ኮንሶ ዞኖች ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በመተባበር ከኮሌጆቹ ለተወጣጡ መምህራን ‹‹Advance Solid Work››፣ ‹‹Basic Solid Work›› እና ‹‹ArchiCAD›› በተሰኙ ሶፍትዌሮች ዙሪያ ከታኅሣሥ 10-14/2015 ዓ/ም የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ሠልጣኞች በቴክኖሎጂ አቅማቸውን በመገንባት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ወደ ማኅበረሰቡ ማሸጋገር እንዲችሉ በየዓመቱ የሚዘጋጅ ሥልጠና ነው፡፡ በመሆኑም ሠልጣኞች ክሂሎታቸውን ማስፋትና በየተቋማቸው ሄደው ለተማሪዎቻቸው የሠለጠኑትን በተግበር ሠርተው ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኮሌጅ ም/ዲን አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል በበኩላቸው ሥልጠናውን የሚወስዱት በዋናነት በቀጥታ ከሙያው ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች ሲሆኑ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትግበራ ክፍተታቸውን ለመሙላት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ በመሆን የሚሰጥ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካል ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና አሠልጣኝ አቶ አዳነ ካሳ ሠልጣኞች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የሶፍትዌሮቹ ክሂሎት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በሶፍትዌሮቹ አጠቃቀም ዙሪያ ያገኙትን መሠረታዊ  ዕውቀት በራሳቸው ማዳበር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ሌላኛው አሠልጣኝ መምህር አቶ ምንተስኖት ካሣሁን በበኩላቸው ሥልጠናው ሶፍትዌሩን በተግባር እንዲጠቀሙ መሠረታዊ ዕውቀት የሚያስጨብጥ ሲሆን ሕንፃዎችን ዲዛይን ማድረግ፣ ሕንፃው ከመገንባቱ በፊት ምን ይመስላል የሚለውን መለየት፣ ሕንፃን በማየት መንገድ በ‹‹ArchiCAD›› በቀላሉ ዲዛይን መሥራት የሚቻልበትን መንገድ በመለየት በገንቢውና በዲዛይነሩ መካከል ያለውን ክፍተቶች ይሸፍናሉ ብለዋል፡፡

ሠልጣኞች ለሥልጠናው የተሰጠው ጊዜ አጭር ቢሆንም ሥልጠናው በሶፍትዌሮቹ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለውን የክሂሎት ክፍተት ለመሙላት ትልቅ ሚና ስላለው መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው አንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ በሥልጠናው መጨረሻ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ለሥልጠናው ተሳታፊዎች የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

                                                                                                                                                                                                                                               የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት