Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂና  ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩቶች ጋር በመተባበር “የጋሞና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የቱሪስት ቦታዎች የካርታ ሥራ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የዲጂታል ኢኮኖሚ ለውጥ ድጋፍ” /Developing Tourist Sites Map of Gamo and South Omo Zones for Supporting Ethiopian Digital Economy Transformation/ በሚል ርዕስ ለ 1 ዓመት ሲከናወን የነበረው የሦስትዮሽ የምርምር ትብብር ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ ወርክሾፕ ታኅሣስ 22/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ  እንደገለጹት  ቱሪዝም ለሀገር ዕድገት ካለው የላቀ ፋይዳና ከአምስቱ የመንግሥት ሀገራዊ የትኩረት መስኮች አንዱ እንደመሆኑ በዘርፉ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመለየትና መፍትሔዎችን ለማምጣት በጋራ ተቀርጾ ሲከናወን የነበረው የፕሮጀክት ሥራ መፍትሔዎችን ይዞ ለፍጻሜ መድረሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በቀጣይ ሀገርንና ሕዝብን የሚጠቅሙ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ከኢንስቲትዩቶቹ ጋር በጋራ ለመሥራት ዩኒቨርሲቲው ቁርጠኛ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው ያረጋገጡ ሲሆን አክለውም ፕሮጀክቱ በውል ስምምነቱ መሠረት በውጤት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የ10 ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመደገፍ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ በበኩላቸው  ፕሮጀክቱ በቆይታ ጊዜው የቱሪዝሙን ዘርፍ በምን መልኩ ይደግፋል ከሚለው እሳቤ በመነሳት ከደቡብ ክልል ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለባቸውን የጋሞና የደቡብ ኦሞ ዞኖች በመምረጥ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ወደ ፊት የቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ቦታዎችን፣ የመንገድ ስርጭትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የመለየት፣ ካርታዎችን ማዘጋጀት፣ የቱሪስት መዳራሻ ቦታዎችን መረጃ ማጠናከር እንዲሁም ዌብ ጂ አይ ኤስ እና ሞባይል አፕሊኬሽን የተባሉ ቴክኖሎጂዎችን ማበልጸግ፣ ማልማትና ለተጠቃሚው ተደራሽ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ለዚህም ሥራ ለሦስቱ ተቋማት ከ3.67 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት እንደነበርም ዶ/ር ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡ የቱሪዝሙን ዘርፍ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የተገኙት መረጃዎች በዶክመንት ደረጃ የተዘጋጁ ሲሆን በቀጣይም አንዳንድ መረጃዎችን የማጥራትና የማሟላት ሥራ እንደሚካሄድ ዶ/ር ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት አማካሪና የዋናው ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ቱሉ በሻ ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር በሁለቱ ተቋማት መካከል የታሰቡ ሥራዎች በታቀደላቸው መርሃ ግብር መሠረት መሠራት እንዲችሉ የተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮችና ተመራማሪዎች ቁርጠኛ ሆነው የታሰበውን በማሳካት ውጤቱ ላይ በመድረሳቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ትልቅ ስኬትም ነው ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡ በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጋር የሚሠሩ ተመሳሳይ ሥራዎች እንዲሁ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተቋማቱ ተመራማሪዎችን በሰው ኃይልና በፋይናንስ አጠናክረን የተሻለ ሥራ በመሥራት የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ፣ በትምህርትና አቅም ግንባታ ዘርፍ የተጠናከረ ትብብር እንዲፈጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ቱሉ አክለውም በተለይም የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በመተባበር ይህን የትብብር ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ማሻገር እንደሚያስፈልግና ተቋማቸውም ይህንን ግንኙነት ለማሻገር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ቱሉ ገለጻ የተገኙት መረጃዎች ክልሉ ለሚሠራቸው የቱሪስት መስህብ ልማት እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ለሚሠሩ ትልልቅ የቱሪስት መሠረተ ልማቶችና መስህቦች እንደመነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተለይ ወደ ደቡብ ክልል የሚመጡ ቱሪስቶች የቱሪስት መስህብ ቦታዎች መገኛዎችን፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ቱሪስት በአካባቢው ያሉ አስቻይ መሠረተ ልማቶች ምን እንደሚመስሉና በጉብኝት ጊዜም የሚፈልጉትን አገልግሎት የት ማግኘት እንደሚችሉ በቂ መረጃ የሚሰጥና በሁለቱ ዞኖች ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሚያደርግ “GoTravel” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ በልጽጎ ተግባራዊ እንዲደረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፕሮጀክት አባላት የተሠራውን የጥናት ውጤት ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል መ/ርና ተመራማሪ ዶ/ር አብረን ገላው የፕሮጀክቱን ዓላማ አስመልክተው እንደተናገሩት በጋሞና ደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን መረጃ የተሳለጠ ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማዘጋጀትና መስህቦቹን ቱሪስቶች በቀላሉ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት መሆኑን  አመላክተዋል፡፡ 

ዶ/ር አብረን በተጨማሪም በዞኖቹ እስካሁን ያልተጎበኙ በርካታ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህብ ያለባቸው ሥፍራዎች መኖራቸውን ጠቁመው ለዚህም የመንገድ አለመኖር፣ የሆቴልና መሰል አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችል መሠረተ አውታር አለመኖርና የመረጃዎች በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ አለመሆን  ዋነኛ ምክንያት ሆነው ቆይተዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የደቡብ ክልል ቱሪዝም ቢሮና የቱሪዝምና ካልቸር ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እነዚህ የቱሪስት መስህቦች የቱሪዝም ሀብት እንዲሆኑ መንገድ እንዲዘረጋ፣ ቱሪስቱ በሚቆይባቸው ቦታዎች ለቆይታው የሚያስፈልጉትን አገልግሎቶች ያገኝ ዘንድ በአካባቢው የሆቴልና ሌሎች ማረፊያ ቦታዎች እንዲሠሩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ዶ/ር አብረን አሳስበዋል፡፡ በቀጣይም በፕሮጀክቱ የተለዩትን ለቱሪዝም መስህብ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለመንግሥት፣ ለሀገር ብዙ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ወደቱሪዝም ለመቀየር መንግሥት ትኩረት አድርጎ ቢያለማ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም ዶ/ር አብረን ተናግረዋል፡፡

መረጃዎቹ ትርጉም የሚኖራቸው ወደመሬት ወርደው ኅብረተሰቡ ሲጠቀምባቸው ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በፕሮጀክቱ ላይ የተሳተፈው ቡድን ወደኋላ ተመልሶ ነገሮችን በጥልቀት በማየት አክሽን ፕላን እንዲያዘጋጅና ለዞኖቹና ለዞን ባህልና ቱሪዝሞች የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን በመስጠት የባለቤትነት ስሜት መፍጠርና አቅማቸውን አጎልብተው ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ሂዳትም በጋሞ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች 358 የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች መለየታቸውን በጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል የጂ አይ ኤስ (GIS) ባለሙያ የሆኑት መ/ር ኃ/ማርያም አጥናፉ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በቀረቡት ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተወካይና ኤክስፐርቶች፣ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ ተወካይ፣ የጋሞ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከተመረጡ ወረዳዎች የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎች እንዲሁም አስጎብኚ ድርጅቶች እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት