Print

‹‹በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና›› በሚል ርእስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከታኅሣሥ 24-27/2015 ዓ/ም የሚቆይ ሀገራዊ የውይይት መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በመድረኩ ለውይይት መነሻ የቀረበው ሰነድ ባለፉት 4 ዓመታት በሀገሪቱ ያጋጠሙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች፣ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞና የተገኙ ስኬቶች፣ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ስኬቶች፣ ቀጣይ የርብርብ መስክና የምሁራን ሚና እና ምሁራንን የማወያየት አስፈላጊነት የሚሉ ሃሳቦችን አካቷል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በዓለም ዓቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምሁራን ለአንድ ሀገር ቀጣይነትና እድገት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረው የውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች የሚገኙበት ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ሀገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዓመታት የመንግሥት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው አሁን ላይ እንደ ሀገር የገጠማትን ችግር በማስወገድና የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ምሁራን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ መድረኩ ለሀገሪቱ ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና የሚሆኑ ገንቢ ሃሳቦች ተደራጅተው ለመንግሥት የሚቀርቡበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደገለጹት ሀገር የጋራ እንደመሆኑ የሁሉንም አካል ተሳትፎ የሚፈልግ ሲሆን ምሁራን በዕውቀት ላይ ተመሥርተው ማኅበረሰቡን በመምራት ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ አቶ ብርሃኑ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎች ምቹና በቀጠናዋም ሆነ በዓለም ተጽዕኖ መፍጠር የምትችል ሀገር እንድትሆን ያመለጡንን ዕድሎች አካክሰን ተቀራርበንና ተግባብተን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችን ጠቅሰው አስተያየታቸውን ሲሰጡ ምሁራን በሀገር ግንባታ ላይ ቀላል የማይባል ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡ ባደጉት ሀገራት ምሁራን በሚያመነጩት ሃሳብ ሀብታቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ሀገራቸውን ለደረሰችበት እድገት እንዳበቋትም ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የጋሞና ጎፋ ዞኖች አስተዳዳሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችና የካውንስል አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት