Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና ክርስቲያን ኤይድ የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በገቡት ውል መሠረት ዩኒቨርሲቲው የእንሰት አመራረትና ማብላላት ሂደትን የሚያሻሽሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አምርቶ ታኅሣሥ 22/2015 ዓ/ም ለድርጅቱ አስረክቧል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ ከድርጅቱ በተገኘ 3.2 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ የተመረቱ ሲሆን በወላይታ ዞን እንሰት አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የሚሰራጩ ናቸው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ ቴክኖሎጂዎቹ እንሰትን ለምግብነት በማዘጋጀት ሂደት ያለውን ከፍተኛ የሥራ ጫና፣ የምርት ብክነትና የምግብ ጣዕም ብልሽት የሚያስቀሩ መሆናቸውን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂዎቹን እንደ ሀገር ለማስተዋወቅና ለማስፋት ለያዘው ውጥን ከክርስቲያን ኤይድ ጋር በትብብር የተሠራው ሥራ አበረታች ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በኩል 2.5 ሚሊየን ብር መድቦ ቴክኖሎጂዎቹን በጋሞ ዞን ደጋማና እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ለማላመድና ለማስተዋወቅ ፕሮጀክት ቀርጾ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ መሰል የትብብር ሥራዎች ቴክኖሎጂዎቹን በሌሎች አካባቢዎች ለማዳረስ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡

እንሰት እንደ ሀገር ተገቢውን ትኩረት ያላገኘ ተከል መሆኑን ያወሱት ተ/ፕ በኃይሉ ከዚህ አንፃር ዩኒቨርሰቲው በቅርቡ እንሰትንና በዩኒቨርሲቲው የተሠሩትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚያስተዋውቅና ተክሉ እንደ ሀገር ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ለማስቻል ያለመ ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ያሳተፈ ዓለም አቀፍ የእንሰት ኮንፍረንስ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶችን ያጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክርስቲያን ኤይድ የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ ይጥና ተካልኝ በበኩላቸው ከ25 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ለምግብነት የሚጠቀሙት እንሰት እንደ ሀገር ተገቢውን ትኩረት ያለገኘ ሲሆን የአመራረትና የማብላላት ሂደቱ ያልዘመነ በተለይም የሴቶችን አድካሚ የጉልበት ሥራ የሚፈልግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሰቲ ይህንን ችግር በመገንዘብ ያከናወናቸው ምርምሮችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ችግር ፈቺዎች ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ ከዩኒቨርሲቲው የተረከብናቸው ቴክኖሎጂዎች የእንሰት አመራረት ሂደትን ስር ነቀል በሆነ መልኩ የሚቀይሩ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ቴክኖሎጂዎቹን በስፋት አምርቶ በሁሉም እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ከተቻለ ከእንሰት የሚዘጋጁ ምግቦችን ከቤት ፍጆታነት ባለፈ ለሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ድርጅታቸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመስኩ የጀመረውን የትብብር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ ይጥና ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂዎቹን በስምምነቱ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት አምርቶ በማስረከቡም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ድርጅታቸው ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚውለውን የገንዘብ ድጋፍ ከአውሮፓ ኅብረት ያገኘ ሲሆን ‹‹ሶ ሳህል›› የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጀት ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ የሚያሸጋግር መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ምርምርን መሠረት አድርገው የተሠሩትን የእንሰት ቴክኖሎጂዎች በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ለማላመድ ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሠራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ1 ዓመት በፊት ከክርስቲያን ኤይድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም የጀመረው ፕሮጀክት ተጠቃሽ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ቶሌራ በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረትና በተፈላጊው መጠንና ጥራት ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂዎቹን አምርቶ ለድርጅቱ አስረክቧል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁ በቀጣይ መሰል ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ልምድ የተገኘበትና መተማመንን የሚፈጥር እንደሆነም ዶ/ር ቶሌራ አውስተዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ-ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው ውጤታማነታቸው በምርምርና በተግባር የተረጋገጡ የሀምቾ መቁረጫ፣ የሀምቾ መፍጫ፣ የቡላ መጭመቂያ፣ ቆጮን ከቃጫ የመለያ ማሽኖች፣ ከሴራሚክና ፕላስቲክ የተሠሩ የቆጮ ማብላያዎችን፣ የቆጮ መብላላትን የሚያፋጥን እርሾ፣ የቆጮ ሽታንና ጣዕምን የሚያሻሽሉ ቅመሞችንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በስፋትና በጥራት አምርቶ ለርክክብ ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን በማምረት ሂደት ውስጥ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደተደረገ የጠቆሙት ዶ/ር አዲሱ ቴክኖሎጂዎቹን ከማምረት ባሻገር በአጠቃቀምና በማሽኖች ጥገና ዙሪያ ከወላይታ ዞን ለተወጣጡ ወጣቶች በዶርዜ ሥልጠና እንደተሰጠም አውስተዋል፡፡ በቀጣይም መሰል ፕሮጀክቶችን ከድርጅቱ ጋር በትብብር ለመሥራት የታቀደ ሲሆን ፕሮጀክቱ የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ የዩኒቨርሲቲውና የክርስቲያን ኤይድ አመራሮች፣ በፕሮጀክቱ ላይ ለተሳተፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትጋት ሲሠሩ ለቆዩት ለዶ/ር አዲሱ ፈቃዱና ባልደረቦቻቸው በርክክቡ ወቅት ምሥጋና የቀረበ ሲሆን ቴክኖሎጂዎቹ ሥራ ላይ ስለመዋላቸው ዩኒቨርሲቲውም ሆነ ድርጅቱ አስፈላጊውን ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት