Print

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል በ ‹‹Development Economics›› ትምህርት ፕሮግራም የ3 ዲግሪ ተማሪ ዕጩ ዶ/ር ኤዞ ኤማኮ ማክሰኞ ታኅሣሥ 25/2015 ዓ/ም የምርምር ሥራውን የውጪና የውስጥ ገምጋሚዎችና አማካሪዎች በተገኙበት አቅርቧል፡፡ የመመረቂያ ጽሑፉም አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ ተመራቂው ለትምህርት ክፍሉ የመጀመሪያ ተመራቂ የሚሆን ሲሆን በአራት ዓመት የቆይታ ጊዜ በጥሩ ውጤት ትምህርቱን ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎች ተማሪዎችም ጥሩ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልጸው ለግምገማ የቀረበው የመመረቂያ ጽሑፍም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል ጥናት ነው ብለዋል፡፡

የድኅረ ምረቃ ት/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ነብዩ የማነህ በ3 ዲግሪ ደረጃ የሚሠሩ ምርምሮች ጠንከር ያሉና በዋናነት ሀገራዊ ችግሮችን እንዲፈቱ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸው የምርምሮቹ ግኝቶችም ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓትነት እንዲውሉ ለማስቻል ጥራት ያለው የጥናት ጽሑፍ እንዲሠራ በት/ቤቱ በኩል አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግና በቀጣይም ይህንኑ አጠናክረው እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

በወርልድ ባንክ የደቡብ ሱዳን ካንትሪ ኢኮኖሚክስትና የውጪ ገምጋሚ ዶ/ር ዘሪሁን ጌታቸው እንደገለጹት ጥናቱ ደረጃውንና ወቅቱን የጠበቀና ለሌሎችም መማሪያ ሊሆን የሚችል ሥራ በመሆኑ ለሀገር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

የውስጥ ገምጋሚ የነበሩት የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር መልካሙ ማዳ በበኩላቸው እንደተናገሩት ጥናታዊ ጽሑፉ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የውጭ ኢንቨስትመንት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ከግብርናው  ወደ ኢንዱስትሪ  ለመግባት አስፈላጊውን አቅጣጫ ያሳየ ሳይንሳዊ ጥናት በመሆኑ ጤናማ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመዘርጋት አጋዥ ይሆናል፡፡

ዕጩ ዶ/ር ኤዞ ኤማኮ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ 2 ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ስፔሻላይዜሽን በኢኮኖሚክስ ፖሊሲ አናሊሲስ እና 3 ዲግሪያቸውን በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አጠናቋል፡፡ ዶ/ር ኤዞ ‹‹Foreign Direct Investment and Its Effect on Structural Transformation in Developing Countries.›› በሚል ርዕስ የመመረቂያ ጥናታቸውን  በማካሄድ   ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በታዳጊ ሀገራት ላይ ያለው ተጽዕኖ ለመዳሰስ እንደሞከሩ ገልጸው ባገኙትም የጥናት ውጤት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለታዳጊ ሀገራት መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ለበርካታ ሥራ አጦች  የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማምጣት የሚረዳ፣ የገቢ ምንጭ የሚሆንና የሀገርን ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማምጣት የተመቻቸ ፖለቲካዊ ሁኔታን በመፍጠር ሀገርን ከጦርነትና መሰል ችግሮች በማጽዳትና የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማቅረብ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ በጥናት ውጤታቸው ጠቁመዋል፡፡ ከብርቱ ትግል በኋላም ለዶክትሬት  ዲግሪ መብቃታቸው እንዳስደሰታቸውም ዕጩ ዶ/ር ኤዞ ገልጸዋል፡፡

ዕጩ ዶ/ር ኤዞ የዶክትሬት ዲግሪያቸው በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ከጸደቀ በኋላ የሚያገኙ ሲሆን በመርሃ-ግብሩ ላይ የኮሌጁ ዲን፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የዘርፉ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች  ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት