Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በጎፋና ኮንሶ ዞኖች እና በደራሼ ልዩ ወረዳ በዝናብ እጥረት በተከሰተ ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 2.1 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የምግብ እህል ድጋፍ ከታኅሣሥ 26-28/2015 ዓ/ም በየሥፍራዎቹ በመገኘት አስረክቧል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ድጋፉ በአካባቢዎቹ በዝናብ እጥረት ምክንያት በተፈጠረው ድርቅ የተከሰተውን ችግር በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍና ተረጂዎች የገና በዓልን በመልካም ሁኔታ እንዲያሳልፉ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ለመሰል ችግሮች ለተጋለጡ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት ዶ/ር ተክሉ የአሁኑ ድጋፍም ለሦስቱም አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ 60 ኩንታል በቆሎና 60 ኩንታል ማካሮኒ ያካተተና በገንዘብ ሲተመንም 2.1 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ነው ብለዋል፡፡

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ጌትነት በጋሻው በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት በዞኑ በሚገኙት ዛላ፣ ኡባ ደብረፀሐይና ዴምባ ጎፋ ወረዳዎች በተከሰተ ተከታታይ የዝናብ እጥረት ሳቢያ በተከሰተ ድርቅ ከ155 ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፍተኛ የምግብር እጥረት ተዳርገዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለወገኖቻችን ያደረገው ድጋፍ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው ያሉት ዶ/ር ጌትነት ለተደረገው ድጋፍ በዞኑ ሕዝብና አስተዳደር ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሊሠራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት አስተዳዳሪው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በዋናናት በአካባቢው የሚገኘውን የከርሰ ምድር ውሃ አውጥቶ ለመጠቀም የሚያስችል ጥናትና ምርምር በማካሄድ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኮንሶ ዞን ም/አስተዳዳሪና የንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገልገሎ ገርሾ በዞኑ ባለፉት 3 ዓመታት ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ ባለመኖሩና በአካባቢው በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ችግሩን በመገንዘብ ላዳረገው ድጋፍ በኮንሶ ዞን ሕዝብና መንግሥት ስም ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ገልገሎ ዩኒቨርሲቲው በተለይ በውሃ ምኅንድስና ዘርፍ በርካታ ምሁራንን ለሀገር በማበርከት የሚታወቅ እንደመሆኑ በቀጣይ በአካባቢው ያለውን የገጸ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት መጠቀም የሚያስችሉ ጥናቶችንና ምርምሮችን በማካሄድና የምርምር ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በመሥራት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እንዲሠራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

የደራሼ ልዩ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታኩ ታዮና በበኩላቸው በልዩ ወረዳው በተከሰተ ግጭትና በተለይ በቆላማ አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅ በርካታ ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ ‹‹ለወገን ደራሽ ወገን ነው›› የሚለውን አባባል በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ በአካባቢው በነበረው ግጭት በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ቀውሶች የገጠሙ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም መሰል ድጋፎችን ማድረጉን እንዲሁም በዘላቂ ሰላምና ግጭት አፈታት እና በግብርናና በተፋሰስ ልማት ዘርፎች ምርምሮችንና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኃላፊው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

                                                                                                                                           የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት