Print

ከጋሞ እና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ከደራሼና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ 30 የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የሴቶች ሊግ መካከለኛ ሴት አመራሮች የአመራርነትንና የተግባቦት ክሂሎትን ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና ከጥር 3-4/2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊና የሴቶች ሊግ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምነሽ ደመቀ የሥልጠናው ዋና ዓላማ በሴቶች ሊግ ሥራ አስፈጻሚ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች አንዱ የሴት አመራሮችን የመሪነት ብቃት በማሳደግ ተከታዮችን እንዲያፈሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚ በመሆን ሥልጠናውን በማዘጋጀቱ በሊጉ ስም ለዩኒቨርሲቲው ምሥጋና አቅርበዋል።

ወ/ሮ ዓለምነሽ አክለውም ሀገሩንና ወገኑን ወዳድ አመራር ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ይችላል ያሉ ሲሆን በአስተሳሰብ የጠራ አመለካከት ያለው አመራር ሀገራችን አሁን እያደረገች ያለችውን የፀረ-ድህነት ጦርነትና ከኋላቀርነት የመላቀቅ ትግልን በአሸናፊነት ለመወጣት ያግዛል ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅ/ጉድ/ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሥልጠና እንዲሰጥ በጠየቀው መሠረት ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀው የአመራርነትና የተግባቦት ክሂሎቶች በሥልጠናዎች እየተደገፉ በሥራ ቦታ በተግባር እየተፈተሹ የሚዳብሩ ናቸው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ሥልጠናው ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ሥልጠናዎች መካከል አንዱ ሲሆን በሌሎችም ሥልጠናዎችና ሙያዊ ድጋፍፎችም ጭምር እየተደጋገፍን ለሀገራችን ብልጽግና አብረን መትጋት ይገባል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኅ/ጉድ/አስተባባሪ መ/ርት አስቴር ሰይፉ የአመራር ክሂሎት ማሳደግና ሥነ ተግባቦት የሥልጠናው ይዘቶች ሲሆኑ ሴቶች ወደ አመራር በሚመጡበት ወቅት በግል ሕይወታቸው፣ በማኅበረሰብ አስተሳሰብና አመለካከት ምክንያት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በማለፍ በሥራቸው ብቁና ስኬታማ በመሆን ለሌሎች ሴቶችም አርዓያ እንዲሆኑ ለማስቻል ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ራሳቸውን በዕውቀትና በክሂሎት እንዲያጎለብቱ የተሻለ ግንዛቤ የፈጠረና የዕይታ አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ያገዛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሥልጠናው መጨረሻ ለሠልጣኞች የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት