Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም እየጠፋ ያለውን የኦንጎታ ቋንቋ ለመታደግ በቋንቋው ላይ የምርምር ጥናት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ጥር 7/2015 ዓ/ም ጂንካ ከተማ በሚገኘው የደቡብ ኦሞ ምርምር ማእከል ውስጥ አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ም/ቢሮ ኃላፊና የኃላፊው ተወካይ አቶ ማቴዎስ ሎምበሶ ደቡብ ኦሞ ዞን በክልሉ ሰፊ የቆዳ ሽፋንና በርካታ ማኅበረሰብ ያለበት መሆኑን ጠቅሰው በአካባቢው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ቋንቋዎች እንዳይሞቱና ሕዝቡም ማንነቱን እንዳያጣ ዩኒቨርሲቲው በባለቤትነት መንፈስ ጊዜና በጀት መድቦ ሥራ በመጀመሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡  በተለይም የብራይሌ ብሔረሰብ ቁጥር መመናመን፣ የአንጎታ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር ማነስና ቋንቋው በሌሎች በአካባቢው በስፋት በሚነገሩ ቋንቋዎች እየተዋጠ መሄዱ አሳሳቢ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ማቴዎስ ለተጀመረው ፕሮጀክት ቢሯቸው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የሰው ልጅ እርስ በእርስ የሚግባባበት ዋነኛ ዘዴ የሆነው ቋንቋ በተለያዩ ምክንያቶች ተናጋሪ ሲያጣ ለትውልድ የመተላለፍ ዕድሉ እያነሰ ይመጣል ብለዋል፡፡ ቋንቋ ሲሞት ማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ በርካታ ታሪካዊ፣ መንፈሳዊና ስነ-ምኅዳራዊ ዕውቀት እና ባህሎችን ይዞ እደሚሞት ጠቁመዋል፡፡

እንደ ተ/ፕ በኃይሉ የኦንጎታ ቋንቋ ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ለመታደግ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ በጀት መድቦና የሰው ኃይልን አሰማርቶ ለመሥራት የተነሳ በመሆኑ የደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በሙሉ አቅም መሳተፍና አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተሞክሮው ለሌሎች ተመሳሳይ የመጥፋት አደጋ ለተጋረጠባቸው ቋንቋዎች እንደ ምሳሌ ሊወሰድ የሚችል በመሆኑ በትኩረት እንደሚሠራም ተ/ፕ በኃይሉ ተናግረዋል፡፡

የማኀበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የፕሮጀክት ሥራው በቦታው በመገኘትና ጥናት በማካሄድ እየጠፋ ላለው የኦንጎታ ቋንቋ ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሚሰጥና የዶክሜንቴሽን፣ ቋንቋውን የማሳደግና የማስቀጠል ሥራዎችን እንደሚሠራ ይታመናል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ እንደገለጹት ተቋማቸው እየጠፉ ያሉ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ በርካታ ሀገረሰባዊ ዕውቀቶችና ታሪኮች ላይ ምርምር በማካሄድ ለመሰነድ ብሎም ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል ይሠራል፡፡ በመጥፋት ላይ ያለው የኦንጎታ ቋንቋ ጥናታዊ ምርምር ፕሮጀክትም ቋንቋውን በመሰነድ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እና በቋንቋው ውስጥ ያሉ ብዝሃ ማንነቶችን ለሌላው የዓለም ክፍል እንዲደርስ ለመሥራት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ ባቀረቡት ቁልፍ ንግግር በዞኑ 16 ብሔረሰቦች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ባህላቸውና ቋንቋቸው አድጎ ለትምህርት የዋሉት ጥቂቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የብሔረሰቦቹን ማንነት፣ ቋንቋና ባህል በማጥናት የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የምሁራን ሚና የላቀ መሆኑን የጠቀሱት አፈ ጉባኤዋ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቱን ይዞ በመምጣቱ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በብራይሌ ብሔረሰብ በተለይ በኦንጎታ ቋንቋ ላይ ለሚደረገው ጥናትም ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ ባቀረቡት የአንጎታ ስነ-ቃላዊ ተረኮች የይዘት ትንታኔ እንደተመለከተው ተሰብስበው የተጠኑ ተረቶች የአንጎታን ቋንቋ ተናገሪ ማኅበረሰብ የእህትማማችነትና የወንድማማችነት ስሜት፣ በሰላም አብሮ የመኖር፣ እርስ በእርስ መተማመንና መከባበር እሴቶች የሚያሳዩ ናቸው፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ት/ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ስንታየሁ ሰሙ የኦንጎታ ቋንቋ የመጥፋት ምክንያቶች፣ በቀጣይ ቋንቋውን ለማትረፍ ሊሠሩ የሚገቡ ጉዳዮችንና አጠቃላይ በፕሮጀክቱ የቆይታ ጊዜ የሚከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ የተለያዩ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ የኦንጎትኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በ2007 ዓ/ም 15 እንደነበሩና በአሁኑ ወቅትም ቋንቋውን በትክክል የሚናገሩ ከ3-5 የሚደርሱ ሰዎች ብቻ መቅረታቸውን ጠቁመው ጉዳዩ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ዛሬ ነገ ሳይሉ ወደ ሥራው እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ክፍል ለ3 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ለሥራው ማስፈጸሚያ ዩኒቨርሲቲው አንድ ሚሊየን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺ ብር የመደበ መሆኑንም ዶ/ር ስንታየሁ ጠቁመዋል፡፡

የቋንቋው ተናጋሪዎች በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው በቋንቋው ምንም ተናጋሪ ከማጣታችን በፊት ደርሶልናልና ጥናቱን ወደተግባር በመቀየር ሕፃናት ቋንቋውን እንዲለምዱና በሥልጠናና በተለያዩ ድጋፎች የተናጋሪው ቁጥር እንዲጨምር ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች የፕሮግራሙ ታዳሚዎች ቋንቋው ሊያንሰራራ የሚችለው በምሁራንና በአጥኚዎች ብቻ ሳይሆን በቋንቋው ተናጋሪዎችና ተወላጆች ከፍተኛ ጥረት ጭምር በመሆኑ ቋንቋውን ለመታደግ ሁሉም የድርሻውን  ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ የብራይሌ ብሔረሰብ ሽማግሌዎችና የኦንጎታ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ፣ ከደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ ከደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር፣ ከጂንካ ከተማ፣ ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ፣ ከበና ፀማይ አስተዳደር፣ ከበና ፀማይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከብራይሌ ማዘጋጃ ቤት የተወጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት