Print

በ"AMU-IUC" ፕሮግራም 2 ዙር ቤልጂየም ሀገር በሚገኙ 5 ዩኒቨርሲቲዎች የ3 ዲግሪ ትምህርት ዕድል ላገኙ ተማሪዎች የትውውቅና የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ጥር 5/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ


የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንትና የ"AMU-IUC" ፕሮግራም የሀገር ውስጥ አስተባባሪ ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በፕሮግራሙ 2ኛ ዙር 14 የዩኒቨርሲቲው መምህራን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የትውውቅ መርሃ ግብሩ ተማሪዎቹ ስለፕሮጀክቱ አሠራሮች ግንዛቤ የሚያገኙበት፣ ከቀድሞ ተማሪዎች ልምድና ተሞክሮ የሚቀስሙበት፣ እርስ በእርስ የሚተወወቁበትን ዕድል የሚያመቻችና በቀጣይ የትምህርት ቆይታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ጠቃሚ መረጃዎችን የሚያገኙበት መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡

የ"AMU-IUC" ፕሮግራም ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በበኩላቸው የትምህርት ዕድሉን ያገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በውጭ ሀገር እንደመሆኑ በቆይታቸው ሊገጥሟቸው በሚችሉ ችግሮች፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ መስተጋብር እና በትምህርትና ምርምር ሥራቸው ወቅት ትኩረት ማድረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መርሃ ግብር እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ከትውውቅ ባሻገር በ2ኛው ዙር የፕሮግራሙ የ5 ዓመታት ቆይታ ሥርዓተ ጾታን መሠረት አድርጎ የሚሠራውን 7ኛውን አዲስ ፕሮጀክት ማስተዋወቅና የተሻሻሉ አዳዲስ አሠራሮች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ሌላኛው የመርሃ ግብሩ ትኩረት መሆኑን አውስተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በበይነ መረብ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የፕሮግራሙ የውጭ አስተባባሪ ፕ/ር ሮል ማርክስ  የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች የፕሮግራሙ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ተናግረው ተማሪዎቹ ቤልጂየም ሀገር በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የ"IUC" አባላት ከጎናቸው እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ የዶክትሬት ዲግሪ ባለቤት መሆን ሙሉ ተመራማሪና ሳይንቲስት የመሆን ምዕራፍ የሚጀመርበትና ትልቅ ኃላፊነት የሚኖርበት በመሆኑ ተማሪዎች ይህንን በመገንዘብ ትምህርታቸውን በስኬት ለማጠናቀቅ በርትተው ሊሠሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ በ"AMU-IUC" የመጀመሪያ ዙር ፕሮግራምና በሌሎች መሰል ፕሮጀክቶች ትምህርታቸውን በቤልጂየም ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ይጠቀሳሉ፡፡ ዶ/ር አዲሱ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ስኬታማ ለመሆን ጌዜያቸውን በአግባቡ ማስተዳደር፣ በቡድን ሥራዎች ላይ በንቃት መሳተፍ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በአግባቡ መከታተል፣ አማካሪዎቻቸውን እንደ ደጋፊ ብቻ መቁጠር አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህንንና መሰል ተግባራትን በማከናወናቸው ትምህርታቸውን በ3 ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደቻሉ የገለጹት ዶ/ር አዲሱ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላም የተለያዩ ሽልማቶችን ማግኘት እንደቻሉና በዩኒቨርሲቲው 5 ፕሮጀክቶችን በማምጣት እየሠሩ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የ2 ዙር ቆይታ የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ካገኙ ተማሪዎች መካከል መ/ር ዓይናለም ጎቸራና መ/ርት ፍቅርተ ሥዩም በሰጡት አስተያየት በትውውቅ መርሃ ግብሩ ቀጣይ የትምህርት ቆይታቸውን ስኬታማ የሚያደርጉ ልምዶችን እንዲሁም ስለፕሮግራሙ አሠራሮችም ግንዛቤ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ በቀድሞ ምሩቃን የቀረቡ ልምዶችና የስኬት መንገዶች ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረባቸው መሆኑንም አውስተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ አዲስ በተጀመረው በሥርዓተ-ጾታ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በሚሠራው ተጨማሪ ፕሮጀክት ዙሪያ ገለጻ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ፕሮጀክቱ በዋናነት በፕሮግራሙ በሚገኙ 6 ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት የሥርዓተ ጾታ ጉዳይን አካተው እንዲሠሩ ለማድረግና በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ ሴት መምህራንና ተመራማሪዎች ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር የሚሠራ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

                                                                                                                                                                                                                የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት