Print

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤሊያስ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ተመራማሪዎች ጋር በተለያዩ የምርምር ግኝቶች፣ ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችና በትብብር መሥራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ጥር 10/2015 ውይይት አካሂደዋል፡፡ ተጨማሪ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ለውይይቱ መነሻ እንዲሆን በዩኒቨርሲቲው የተከናወኑ ሁለት የምርምር ፕሮጀክቶችና አንድ የምርምር ንድፈ ሃሳብ ዙሪያ የተዘጋጁ የውይይት መነሻ ሠነዶች ቀርበዋል፡፡

በዕለቱ የውሃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ «Joint Collaborative Effort to Save Lake Chamo and its Watershed» በሚል ርዕስ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሠነድ በዩኒቨርሲቲው የተደረጉ ምርምሮችን መሠረት በማድረግ የጫሞ ሐይቅን ህልውና ለማዳን ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አጋር አካላት በመሆን እየሠራ ስለመሆኑ፣ በሐይቁ ተፋሰስ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እንዲሠሩ በተደረገ  ከፍተኛ ጥረት በሁሉም በተጎዱ የተፋሰሱ ሥፍራዎች ላይ በዩኒቨርሲቲው የተደረጉ ምርምሮችን መሠረት ያደረገ ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ፕሮጀክት ስለመገኘቱ፣ የምርምር ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ከ“GIZ” እና ከኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ጋር በመሆን በሐይቁ ዙሪያ የሚገኘውን ረግረጋማ ስፍራ ወደነበረበት ለመመለስ እንዲሁም የጌዣ ጥብቅ ደንን በፈር ዞን /Buffer Zone/ የመለየትና በደኑ ውስጥ በተፈጠረ ሸለቆ ላይ የአፈርና ወሃ ጥበቃ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡   

«Enset the Next Super Food» በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሠነድ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የባዮቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፍቃዱ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የእንሰት ማብላላትና አመራረት ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረጉ የምርምር ሥራዎች  የተገኙትን የቆጮ ማብላላት ሂደትን የሚያፋጥን እርሾና ቆጮን በባህላዊ መንገድ ለማብላላት ጉድጓድ ውስጥ የመቅበር ሂደትን የሚያስቀሩ ቴክኖሎጂዎች እንሰት አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የማስተዋወቅና የማላመድ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አዲሱ ተክሉን ለምግብነት ለማዋል በባህላዊ መንገድ ሲዘጋጅ በእጅጉ አድካሚና ጊዜ ገዳይ የሆነውን የመቁረጥ፣ የመጭመቅና የመፋቅ ሂደትን የሚያዘምኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድና አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙባቸው የማድረግ ሥራም በዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ከቆጮና ከቡላ ዱቄት የሚዘጋጁ ዳቦ፣ ኩኪስ፣ ኬክና ሌሎች እሴት የተጨመረባቸው ምግቦችን ማምረት መቻሉም ሌላኛው የመስኩ ፈጠራ መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው የእንሰት ተክል ካለው ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጠቀሜታዎች አንፃር ተክሉን ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራም ማዋል እንደሚቻል የምርምር ግኝት ውጤቶች እንደሚያሳዩ ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ በአካባቢው በተደጋጋሚ ከሚከሰት የዝናብ ዕጥረት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ድርቅን ምክንያት በማድረግ ለመስኖ ሥራ የሚውል የከርሰ ምድር ወሃ አቅም ማወቅን ዓላማ አድርጎ ጥናት ለማከናወን ያዘጋጀው የምርምር ንድፈ ሃሳብም (Proposal) በዕለቱ በዶ/ር ልዑልዓለም ሻኔ አማካኝነት ለውይይት ቀርቧል፡፡

በቀረቡት የምርምር ግኝቶችና ንድፈ ሃሳቡ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዛላ ወረዳ የከርሰ ምድር ውሃ አቅምን ለማወቅ በዩኒቨርሲቲው ጥናት ለማከናወን መታቀዱ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ችግር የሚፈታ በመሆኑ ከፕሮጀክቱ ጠቃሚነት አንፃር  በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ድጋፍ እንዲኖረው የበኩላቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡ ከእንሰት ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያይዞ በዩኒቨርሲቲው የተደረጉ ምርምሮችና ግኝቶች በእጅጉ እንዳስደሰቷቸው የገለጹት አቶ ኃይለማርያም የተገኙት የምርምር ውጤቶች እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ውጥን ስኬት እንሰት ጉልህ ሚና እንዲጫወት የሚያስችል ስለሆነ መንግሥት ለመስኩ ትኩረት እንዲሰጥ ግኝቶቹን  ለኢፌዴሪ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሚያሳውቁና ጉዳዩንም በቅርበት እንደሚከታተሉ አረጋግጠዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በእንሰት ዙሪያ የተደረጉ የምርምር ግኝቶችን በማስቀጠል እንሰትን የራሱ ብራንድ ለማድረግ በትኩረት እንዲሠራ ያሳሳቡት አቶ ኃይለማርያም በዋናነት በፋውንዴሽኑ በኩል በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ላይ የትብብር ሥራ እንደተጀመረ ሁሉ የቀድሞ ቤታቸው ከሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋርም በትብብር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስና በእንሰት ተክል ላይ ያከናወናቸው ምርምሮችና ግኝቶቹን ወደመሬት ለማውረድ  የጀመራቸው ሥራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በዛላ ወረዳ የከርሰ ምድር ውሃ አቅምን ለማወቅ ሊያደርግ ያሳበው ጥናት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የተናገሩት ፕ/ር እያሱ በመስኩ በግብርና ሚኒስቴር ስር ከታቀዱ ሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር በማቀናጀት ሥራውን በማስፋት በቅንጅት እንሠራለን ብለዋል፡፡ ከእንሰት ጋር ተያይዞ የቀረቡት የምርምር ግኝቶች በእጅጉ እንዳስገረሟቸው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣይ ተክሉን የግብርና ኤክስቴንሽን ሥራ ውስጥ እንዲገባ በመስኩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል፡፡ እንሰትን ማዕከል ያደረገ ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ መሥራት ተክሉ ካለው ተፈጥሯዊ ባህሪና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር ወሳኝ በመሆኑ በቅርቡ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ላይ በሚጀመረው ፕሮጀክት እንሰትን ለዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለመጠቀም መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ አንደ ሀገር ከተለዩ 8 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ በዕለቱ ከቀረቡት ሥራዎች ባሻገር በሌሎች  ርዕሰ ጉዳዮችም ዙሪያ ውጤታማና የማኅበረሰቡን የአኗኗር ሁኔታ የሚያሻሽሉ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ በማኅበረሰብ አገልግሎት በኩልም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተተው ተግባራት ላይ በማተኮር ምርምርን መሠረት ያደረጉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ በዕለቱ የቀረቡት ፕሮጀክቶችም ከዚህ አንፃር የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመስኩ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤሊያስ ጋር የተደረገው ውይይትም ፍሬያማና ለቀጣይ ትብብር ሥራዎች መንገድ የጠረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት