ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ 25 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የጫሞ ሐይቅ ተፋሰስን ወደነበረበት ለመመለስ በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው ፕሮጀክት ስኬታማ እንዲሆን ከጋሞና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ከደራሼ፣ ቡርጂና አማሮ ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ አስተዳዳሪዎችን እና የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኃላፊዎችን ያካተተ የአመራሮች የጋራ መድረክ ጥር 10/2015 ዓ/ም በይፋ ተመሥርቷል፡፡ በዕለቱ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴም የአመራር መድረኩ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ተጨማሪ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዕለቱን መርሃ-ግብር በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ሰብሳቢ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ  በሁለት ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች ባሉ 10 ወረዳዎች የሐይቁን ህልውና ለመታደግ በቅርቡ ከጀርመን ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን አሳታፊና ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ ለ5 ዓመታት በሥራ ላይ የሚቆየው ፕሮጀክቱ ኅብረተሰቡን ማዕከል አድርጎ የሚሠራ ሲሆን ኅብረተሰቡን በማስተባበርና በማንቀሳቀስ ሂደት ውስጥ የአካባቢው አመራሮች የሚኖራቸው ሚና የጎላ በመሆኑ ይህንን የአመራሮች መድረክ መፍጠር አስፈልጓል ብለዋል፡፡ የአካባቢው አመራሮችም ፕሮጀክቱ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ወደነበሩበት ከመመለስ ባሻገር ከሥራ ዕድል ፈጠራና የማኅበረሰቡን የአኗኗር ሁኔታ ከመቀየር አንፃር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

እንደ አቶ ኃይለማርያም ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተደረጉ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎች ሚናቸው የጎላ ሲሆን በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በፕሮጀክቱ አፈፃፃም ወቅት የተጣለበትን በዕውቀትና ሳይንስ ላይ የተመሠረተ የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች በአግባቡ እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር እያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው በተፋሰሱ ላይ የሚጀመረው ፕሮጀክት የሐይቁን ህልውና ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጫሞ ተፋሰስ ላይ የሚሠራው ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሀገር ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ለውጤታማነቱ የአካባቢው አመራሮች ማኅበረሰቡን በተለይ ወጣቶችን በስፋት በማሳተፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ እንደ ግብርና ሚኒስቴርም ጽ/ቤታቸው በፕሮጀክቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ሲገልጹ ከዚህ ቀደም በወዜ ሻራ ተፋሰስ  አሁን ላይ ደግሞ በቤራ ተራራ ላይ እየሠራ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡  ፕሮጀክቱ የሐይቁን ተፋሰስ ሙሉ በሙሉ በሸፈነ መልኩ የአፈርና ውሃ  ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የታቀደ መሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ መሆኑን ያወሱት ፕሬዝደንቱ የአካባቢው አመራሮችም ይህን በብዙ ጥረት የተገኘ ዕድል በአግባቡ መጠቀም አለባቸው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ለፕሮጀክቱ እውን መሆን እንዳደረጉት ጥረት ሁሉ ለአፈፃፀሙም የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ዶ/ር ዳምጠው ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን ችግር ከማውራት ወጥተን ወደመፍትሄው እንድንገባ በር የከፈተ መሆኑን ጠቅሰው በዛሬው ዕለት የተመሠረተው የአመራሮች መድረክም አመራሩ ሥራውን በባለቤትነት ወስዶት እንዲሠራ ያስችላል ብለዋል፡፡ የችግሩን አንገብጋቢነት በመገንዘብ አመራሩ ማኅበረሰቡን የማንቃትና የማስተባበር እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የሚውሉ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በመወሰን ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበው እንደመድረኩ ሰብሳቢነታቸውም የበኩላቸውን ሚና በቁርጠኝነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ"AMU-IUC" ፕሮግራም ማኔጀርና የውሃ ሥነ-ምኅዳር ተመራማሪው ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ብዙ ጊዜ መሰል ፕሮጀክቶች በፖለቲካ አመራሩ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፈጠር ባለመቻሉ ስኬታማ ሳይሆኑ እንደሚቀሩ አውስተዋል፡፡ አሁን ላይ የተመሠረተው የአመራሮች የጋራ መድረክ ማኅበረሰቡን ከማስተባበር አንፃርና ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የተለያዩ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን መውሰድ የሚችሉ አመራሮችን በሥራው ሂደት ላይ በኃላፊነት ስሜት ማሳተፍ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡  እንደዘርፉ ተመራማሪ በግላቸውም ሆነ በሚመሩት ፕሮግራም አማካኝነትና በፕሮጀክቱ ለዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ለፕሮጀክቱ ስኬት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ፋሲል የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ  ሥራው የጫሞ ሐይቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአመራሮች መድረኩ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሂደት ውስጥ ፈጣን ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን የሚወስድ የአስተዳደር መዋቅር ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑ በዕለቱ በቀረበው መመሪያ ላይ ተመላክቷል፡፡ በመመሪያው እንደተመላከተው መድረኩ በፕሮጀክቱ የተያዙ የሥራ ዕቅድና ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ የመሥራትና ቁጥጥር የማድረግ፣ የፕሮጀክቱ አፈፃፀምን በየጊዜው የመገምገም፣ በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሂደት ውስጥ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችንና ማነቆዎችን ለይቶ በፍጥነት የመፍታት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በፕሮጀክቱ ላይ በስፋት መሳተፉንና ተጠቃሚ መሆኑን የማረጋገጥና ሌሎች ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት