የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የዩኒቨርሲቲውን የ2015 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ጥር 12/2015 ዓ/ም ገምግሟል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የትምህርት ጥራት፣ አግባብነት፣ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፤ የምርምር እና ፈጠራ ሥራዎች ተደራሽነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም የሀገር በቀል ዕውቀትን ማጣጣምና ማሳደግ፤ የማኅበረሰብ ጉድኝትና የሳይንስ ባህል ግንባታ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማሳደግ፤ የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ፣ ሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርን እና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማሳደግ፤ የትምህርት አመራርና አስተዳደርን ማጠናከር፤ የትምህርት ተቋማዊ አቅምና ብቃት ማጎልበት፤ ተቋማዊ መሠረተ ልማት፣ ፋሲሊቲን እና ግብዓትን ማሳደግ እና የሀብት ምንጭና አጠቃቀም ውጤታማነት ማሳደግን የትኩረት አቅጣጫዎች በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ዕቅድ የተዘጋጀ መሆኑንና  አፈጻጸሙም በእነዚህ ግቦችና አቅጣጫዎች መሠረት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዕለቱ መርሃ-ግብርም ከትኩረት አቅጣጫዎች ወይም ግቦች አንፃር የቀረበውን የግማሽ ዓመት ሪፖርት በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና ደካማ አፈፃፀም የታየባቸው መስኮችን በመለየት በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ይፍሩ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመላከተው 25  ተጨማሪ የ2ኛ 7 የ3ኛ ዲግሪ ሥርዓተ ትምህርቶች እንዲዘጋጁ መደረጉ፣  ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ለመጡ 54 ተማሪዎች የመጀመሪያና 2ኛ ዲግሪ ነጻ የትምህርት ዕድል መሰጠቱ፣ የቤተ-መጽሐፍት አገልግሎትን ለማሻሻል ሶፍት ኮፒና ሃርድ ኮፒ መጻሕፍቶችን፣ የመመረቂያ እና የምርምር ጽሑፎች ከመምህራን የማሰባሰብና ለንባብ ዝግጁ የማድረግ ሥራ መከናወኑ፣ መስፈርቱን ላሟሉ 3 መምህራን የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መሰጠቱ፣ በዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ-ትምህርት ተገቢነት ለማረጋገጥ በሁሉም ትምህርት ክፍሎች የውስጥ ጥራት ኦዲት ማድረግ፤ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋትና የተለዩ ክፍተቶችን ለማረም አቅጣጫ ተቀምጦ በሙሉ ትኩረት እየተሠራ መሆኑ በአካዳሚክ ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ካለፉት ዓመታት የተሸጋገሩ 50 ምርምሮች መጠናቀቃቸው፣ በሀገር በቀል ዕውቀቶች ዙሪያ 17 ምርምሮች እንዲካሄዱ መደረጉ፣ በዩኒቨርሲቲዉ የምርምር ትኩረት መስክ ለሚሠሩ 8 የድኅረ-ምረቃ የግል ተማሪዎች ምርምሮች የገንዘብ ድጋፍ መደረጉ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር ላይ ያተኮሩ 7 ትልልቅ ፕሮጀክቶች/Grand Research Projects/ ፀድቀው ወደ ሥራ መግባታቸው፣ 3,130 የማኅበረሰብ አባላት ነፃ የሕግ ጥብቅና፣ የምክር አገልግሎትና የሠነድ ዝግጅት አገልግሎት ድጋፍ ማግኘታቸው፣ የተለያዩ 8 የማኅበረሰቡን ችግር ፈቺ የሆኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ እና የአነስተኛ ኃይል ማመንጫ የማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆናቸው፣ ከጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች እና ከደራሼ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ 291 ከ7ኛ-12ኛ ክፍል ተማሪዎች በኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ፣ ሒሣብ፣ ኤሌክትሮኒክስና ICT ትምህርቶች የክረምት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነርንግና ሒሳብ /STEM/ የክሂሎት ሥልጠና መሰጥቱ፣ 8 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ፕሮቶታይፕ የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ፈጣራና ሽግግር እና በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ለአራተኛው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን 25 ሺህ ችግኞች የተተከሉ መሆናቸውና ቀደም ሲል የተተከሉ የከተማ ውበትና ጥላ ዛፎችን እንክብካቤ አጠናክሮ ማስቀጠል መቻሉ፣ በጎፋና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም በደራሼ ልዩ ወረዳ በዝናብ እጥረት በተከሰተ ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ 2.1 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ እህል ጥሬ ዕቃ ድጋፍ መደረጉ፣ በሕክምና ላይ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሚውል 1.5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የብርድ ልብስና አንሶላ ድጋፍ ማድረግ መቻሉ፣ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገነባ ለሚገኝው የጋሞ ባይራ ሞዴል አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የላቦራቶሪ፣ የ"ICT"፣ የመማሪያ ክፍል፣ የመኝታ፣ የመመገቢያ፣ የቢሮ ዕቃዎች ድጋፍ መደረጉ በዚሁ መስክ የተከናወኑ ሌሎች ተግባራት መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የተቋሙን የመዋቅር አደረጃጀት ጥናት ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ትግበራ ሥራዎች መጠናቀቃቸው፣ ከመልካም አስተዳደር አኳያ እስከ 2ኛ ሩብ ዓመት መጨረሻ 28 ቅሬታዎች ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች የቀረቡ ሲሆን 19 ቅሬታዎች ምላሽ እንዲያገኙ መደረጉ፣ በ2ኛ ዲግሪ 15፣ በቴክኒክና ሙያ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 4 104፣ በመጀመሪያ ዲግሪ 94 የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ነፃ የትምህርት ዕድል መሰጠቱ፣ የውስጥ ገቢ ብር  37,765,178.59 መሰብሰቡም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለዩኒቨርሲቲው ከተመደበው 1,172,282,600.00 መደበኛ በጀት 69.26% (811,937,566.66 ብር) ሥራ ላይ መዋሉ የተገለጸ ሲሆን የሰርቪስና የመስክ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ቁጥር ማነስና ከሥራው መጠን ጋር ያለመመጣጠን፣ የተማሪ ምግብ ጥሬ ዕቃን ጨምሮ የግብዓት አቅርቦት የገበያ ዋጋ ንረት፣ ከውጭ የሚገዙ የትምህርትና የግንባታ ግብዓቶች ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ አቅራቢዎች በውል በተቀመጠ ጊዜ መሠረት መፈፀም አለመቻል፣  በዋጋ ንረት ምክንያት የግንባታ ሥራ መቀዛቀዙ በግማሽ ዓመት ውስጥ ካጋጠሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች መካከል ዋንኞቹ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ሥራ ውጤቶችንና የተላመዱና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ የማሸጋገር ሥራ አጠናክሮ መቀጠል፣ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እንዲሁም የአስተዳደር ዘርፍ ሥራዎች በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የመሥራት ደረጃን ለማሻሻል በትኩረት መሥራት፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችን በማበራከትና አሠራሮችን በማሻሻል ገቢን ማሳደግ፣ የተዘጋጀውን የዩኒቨርሲቲውን አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት ጥናት መሠረት የሠራተኛ ምደባ ሥራን ማከናወን፣ የትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳን፣ የዩኒቨርሲቲውን ጆርናሎች እና የትምህርት ፕሮግራሞችን አክረዴት ለማድረግ በትኩረት መሥራት፣ ሪፌራል ሆስፒታል ሥራ ማስጀመር፣ ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና አዲስ የተጀመሩትን ደግሞ በብቃት እንዲሠሩ ትኩረት ሰጥቶ መደገፍ በቀጣይ የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ጊዜ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሠሩ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሆኑ በግምገማ መድረኩ ላይ በአጽንዖት ተገልጿል፡፡


                                                                                                                                   የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት