በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ሥልጠናና ምርምር ማዕከል ከጤና ሚኒስቴርና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር በተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ሀገር አቀፍ ፕሮግራም የመረጃ ጥራት ምዘና ጥናት ለማድረግ በተደረሰ ስምምነት መሠረት በመረጃ ሰብሳቢነት ለተመረጡ የኮሌጁ መምህራን ጥር 16/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ማዕከሉ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር እንደ ሀገር በሽታዎቹን ከመከላከል፣ ከመቆጣጠርና ከማከም አንጻር ፋይዳቸው ጉልህ የሆኑ ጥናቶችን የማድረግ እንዲሁም መረጃዎችን ሰብስቦና ተንትኖ የማቅረብ አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በሠራቸው ሥራዎች ባሳየው መልካም አፈፃፀም ከዓለም ጤና ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራውን ይህን የጥናት ፕሮጀክት ማግኘት መቻሉ በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዕውቅና እያደገ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ዶ/ር ታምሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ታምሩ በማዕከሉ የሚገኙ ተማራማሪዎችም ሆነ ሌሎች የኮሌጁ መምህራን ሰፋፊና የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮችን ለማድረግ ገንዘብና ግብአት አቅርበው በትብብር ሊሠሩ የሚችሉ አጋር አካላትን ማፈላለግ እንዲችሉ በግራንት ማመልከቻ አጻጻፍ፣ ፈንድ ማፈላለግና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ኮሌጁ በቅርቡ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተመራማሪዎች የዩኒቨርሲቲውን አነስተኛ በጀት ከመጠበቅ በተለያዩ መስኮች የትብብር ፕሮጀክቶች ተጻጽፈው በማምጣት ግራንድ ምርምሮችን መሥራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ዶ/ር ታምሩ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር ረ/ፕ ጸጋዬ ዮሐንስ በበኩላቸው የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 20 በሽታዎችን የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች በማለት ለይቶ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሀገራችንም 8 በሽታዎች ተለይተው እየተሠራባቸው መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከእነዚህም መካከል 5ቱን የመድኃኒት ዕደላ በማድረግ ለመከላከል  እንዲሁም 3ቱን ሕክምና በመስጠት የማዳን ስትራቴጂዎች ተነደፈው ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በሽታዎቹን ከመከላከልና ከማከም አንጻር የሚሠሩ ሥራዎች ከጤና ኬላ ጀምሮ መረጃዎች በአግባቡ ሪፖርት መደረግ አለባቸው ያሉት ረ/ፕ ጸጋዬ ነገር ግን እንደ ሀገር በመስኩ የሚወጡ መረጃዎች በአብዛኛው የተሟሉና ትክክለኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ረ/ፕ ጸጋዬ የትክክለኛ መረጃዎች መኖር በሽታዎቹን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ብሎም ከማከም አንፃር ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍና እርምጃዎችን ለመውሰድ ስለሚያግዝ የዓለም ጤና ድርጅት ሀገራት በመስኩ ያከናወኗቸው ተግባራት ሪፖርት በየዓመቱ እንዲገመገም አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሠረት ማዕከሉ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በገባው ውልና ባገኘው የ3 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ በሀገሪቱ 9 ክልሎች በሚገኙ 12 ወረዳዎች በተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ዙሪያ ያሉትን መረጃዎች ጥራት ከተለያዩ መስፈርቶች አንጻር የሚገመግም ጥናት ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ ነው፡፡በመረጃዎቹ ላይ የሚታዩ ችግሮችን መለየትና የመፍትሔ ምክረ ሃሳቦችን ማቅርብ የጥናቱ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን የገለጹት ረ/ፕ ጸጋዬ  ይህም እንደ ሀገር በሽታዎቹን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንጻር ትልቅ ግብአት ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡

በጥናቱ ላይ ለሚሳተፉ መረጃ ሰብሳቢዎች የተሰጠው ሥልጠናም የጥናቱን ዓለማ ለማስገንዘብና በመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችና በተዘጋጁ የመረጃ መሰብሰቢያ ቅጾች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች በዋነኛነት በሞቃታማ አካባቢዎች የሚገኙ፣ ድሃውን ማኅበረሰብ በስፋት የሚያጠቁና በአብዛኛው ሴቶችንና ሕፃናትን የሚጎዱ ናቸው። በሽታዎቹ ከአንድ ቢሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የጤና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደሚያስከተሉ መረጃዎች ያመለከታሉ። በዓለማችን በየዓመቱ 2 መቶ ሺህ ሰዎች በእነዚህ በሽታዎች ሳቢያ እንደሚሞቱና 19 ሚሊየን ያህሉ ደግሞ ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች የሚያመላክቱ ሲሆን ድርጅቱ በሽታዎቹን ለመከላከል፣ ለማስወገድና ለማጥፋት እ.ኤ.አ ከ2021-2030 የሚቆይ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

                                                                                                                          የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት