አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Regional Consultative Workshop on Constraints and Opportunities of Sorghum Production in the Southern Ethiopia›› በሚል ርዕስ አርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ፣ የማላመድና የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጡ የማገዝ ፕሮጀክት መክፈቻ ወርክሾፕ ጥር 13/2015 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዕለቱ ቁልፍ ንግግር አቅራቢ አሜሪካ የሚገኘው የካንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ/Kansas State University/ ‹‹Feed the Future Innovation Lab for Collaborative Research on Sorghum and Millet›› ረዳት ዳይሬክተር አቶ ናትናዔል ባስኮም (Mr. Nathanael Bascom)  እንደገለጹት ተቋማቸው ባለፉት 10 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማሽላን የተመለከቱ የምርምርና ልማት ፕሮግራሞችን ቀርፆ እየሠራ ነው፡፡ ማሽላ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በስፋት የሚመረት ሰብል መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ተቋማቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ማኅበራት ጋር ፕሮጀክት ቀርጾ በትብብር እየሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በዘርፉ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን መስጠትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የማሽላን ምርትና ምርታማነት ማሳደግና የእሴት ሰንሰለት ሥርዓትን ማጎልበት የተቋሙ ዋነኛ የሥራ ትኩረት መሆኑንም ረዳት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ አቶ ናትናኤል አክለውም ተቋማቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥነ ምኅዳር ውስጥ መብቀል የሚችሉ ዝርያዎችን የመለየት እንዲሁም በሽታን የሚቋቋሙ የማሽላ ዝርያዎችን መለየትና ማስተዋወቅ ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው በተደጋጋሚ ለድርቅ ከሚጋለጡ ቦታዎች አንዱ በሆነው አካባቢ የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለውን የማሽላ ሰብል በማሻሻል ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በወርክሾፑ የተገኙ ዓለም አቀፍ፣ የሀገር ውስጥ፣ የክልሎች እና የአካባቢው ባለድርሻ አካላት በማሽላ ሰብል አቅም እና ችግሮች ላይ ባደረግነው ውይይት ተመርኩዘን ትልቅ አቅም ያለው ፕሮጀክት እንደምናደርገው አምናለሁ ያሉት ፕሬዝደንቱ በአካባቢው ያለውን የማሽላ ሰብል ምርት አቅም እና ችግሮችን በመለየቱ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ግንባር ቀደም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል መምህር አቶ አሸናፊ ዱጉማ የጥናት ቡድኑ በዋናነት ዝናብ አጠር በሆኑ ጎፋና ዛላ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ መሠረት አድርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ለመቅረፍ ምርታማና ድርቅን ተቋቁመው የተሻለ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ የማሽላ ዝርያዎችን በመምረጥ መነሻ ጥናት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ መነሻ ጥናቱ በደቡብ ክልል 10 ወረዳዎች ውስጥ 30 ቀበሌያትን ያካተተ ሲሆን ለ150 አባወራዎች ቃለ መጠይቅ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የዕፅዋት ሳይንስ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ዘነበ መኮንን እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ ዓላማ የተላመዱ፣ ምርትና ምርታማነታቸው የተሻለና ድርቅን የሚቋቋሙ የእንሰት ዝርያዎችን በደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ እና ጎፋ ቆላማ አካባቢዎች ማላመድ እንዲሁም የእንሰት ተዋጽኦ ምግብ ዓይነቶችና የአመራረት ቴክኖሎጂዎችን ለእርጥበት አጠር ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን የምግብ ዋስትናና የመኖ እጥረት  ችግሮችን መቅረፍ ነው፡፡

በተጨማሪም በእንሰት ዝርያ ስነ-ምኅዳር፣ ምግብ እና መኖ ይዘት ማሻሻል እንዲሁም ማቀነባበርና እሴት መጨመር ዙሪያ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ሥልጠና በመስጠት እንዲሁም በእንሰት ምርምርና ስርጸት ዙሪያ የባለድርሻ አካላትን ትብብር በማሳደግ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ላይ የተመሠረተ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ማፍለቂያ ተመራጭ ተቋም እንዲሆን መሠረት መጣል ፕሮጀክቱ ዓላማ ካደረጋቸው ዝርዝር ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆኑን ዶ/ር ዘነበ ገልጸዋል፡፡

በወርክሾፑ የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የአርባ ምንጭ ግብርና ምርምር ማዕከል ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በግብርና ምርምር ማዕከልና በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ቡድን የተጠኑ የተለያዩ የመነሻ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

                                                                                                                                        የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት