Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ጥናት ኢንስቲትዩት፣ አሜሪካ ሀገር ከሚገኘው ‹‹Alabaster International››፣ ከኬንያው ጆሞ ኬንያታ የግብርናና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና ከ‹‹Girl Child Network›› ጋር እንሰትን በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ለማስታዋወቅና የምግብ ዋስትና መፍትሔ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ ፕሮጀክት ቀርጸው ለመሥራት ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቁ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ተቋማቱ በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ የሚገቡ ሲሆን ከተቋማቱ የመጡ የሥራ ኃላፊዎች በመስኩ የተሠሩ የምርምር ሥራዎችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የዘርፉ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ከጥር 17-19/2015 ዓ/ም የመስክ ምልከታና የጋራ ውይይት አካሂደዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው እንሰትን ከደቡብ፣ ከደቡብ ምዕራብና ከመካከለኛው ኢትዮጵያ ባሻገር በሰሜን የሀገሪቱ ክፍሎች የማስተዋወቅና የማላመድ ሥራ ከኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እየሠራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአራቱ ተቋማት ጋር ሊሠራ ያሰበው የትብብር ፕሮጀክት 3 ሀገሮችን አጣምሮ የያዘ ሲሆን ሥራው እንሰት የአፍሪካውያንን የምግብ እጥረት እንደሚፈታና አፍሪካን መመገብ እንደሚችል በአጋር አካላቱ እምነት የተጣለበት ነው ብለዋል፡፡

እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ከተቋማቱ ጋር የሚሠራው ፕሮጀክት የሰነዶች ዝግጅት እየተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡም የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሜሪካ የሚገኙ 3 ዩኒቨርሲቲዎች በመስኩ ከዩኒቨርሲቲያችን ጋር በትብብር የመሥራት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ ይህም እንሰት ወደ ምዕራቡ ዓለም ጭምር የሚገባበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ያመላክታል ብለዋል፡፡

የ‹‹Alabaster International›› መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚሶስ ሻኖን ፌርናንዶ /Mrs. Shannon Fernando/ ድርጅታቸው መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገ በጤና፣ ትምህርትና ምግብ ዋስትና ላይ በማተኮር የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስለ እንሰት ከ‹‹Franc 24›› ቴሌቪዥን ላይ ባዩት መረጃ መሠረት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመስኩ ተመራማሪ የሆኑትን የዶ/ር አዲሱ ፈቃዱን አድራሻ አፈላልጎ በማግኘት ከተመራማሪው ጋር ንግግሮችን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በጉብኝታቸው እንሰትን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳዩና እንሰት በባህላዊ መንገድ ያለውን አዘገጃጀት እንዲሁም ከዚህ ቀደም በነበራቸው የበይነመረብ ውይይቶች በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የሰሟቸውን ዩኒቨርሲቲው በመስኩ እያላመዳቸው የሚገኙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የምርምር ውጤቶችን በአካል ማየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንሰት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሚስተዋለውን የምግብ ዋስትና ችግር ከመቅረፍ አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት በጉብኝታቸው የላቀ ግንዛቤ እንዳገኙ የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚዋ በቀጣይ ድርጅታቸው እየተቀረጸ በሚገኘው ፕሮጀክት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚሲስ ሻኖን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመስኩ ያከናወናቸው የምርምር ሥራዎች የማኅበረሰቡን አኗኗር የሚያሻሽሉና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያረጋግጡ እንደሆኑ ማየት የቻሉ መሆናቸውንና በተለይ ዩኒቨርሲቲው በዶርዜ የሚገኙ ሴት እንሰት አምራቾችን በማደራጀት የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ ተቋማቸው የዩኒቨርሲቲው ሥራ ዘላቂ እንዲሆንና እንዲሰፋ በትብብር የመሥራት ፍላጎት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዋ በጤናው ዘርፍም በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ከተቋማቱ የመጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ቀደም ብሎ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸው አሁን ላይ ከዚህ ቀደም በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የተነገራቸውን በተግባር ለማየት እንዲሁም በቀጣይ በመስኩ ለመሥራት ለታሰበው የትብብር ፕሮጀክት ዕቅድ ለማዘጋጅት እንደመጡ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ሊሠራ የታሰበው ፕሮጀክት እንሰትን ተክሉ ባልተለመደባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የማዳረስና የኢትዮጵያን ጥቅምና መብት ባስከበረ መልኩ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጭምር ለማባዛት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ኬንያን ጨምሮ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የጫካ እንሰት መኖሩን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ በዚህ የጫካ እንሰት ዙሪያ ምርምሮችን ማካሄድ ሌላኛው የፕሮጀክቱ ትኩረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በጋራ ለመሥራት የተዘጋጁት ተቋማት ለታሰበው ፕሮጀክት አስፈላጊውን የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንና ፕሮጀክቱ ተግባር ላይ ሲውል እንሰት ቀጣዩ የዓለማችን ዋነኛ ምግብ ይሆናል ተብሎ ለተያዘው ውጥን መንደርደሪያ እንደሚሆን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

የ‹‹Girl Child Network›› ዋና ሥራ አስፈጻሚና የጆሞ ኬኒያታ የግብርናና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን በመወከል የተገኙት ሚሲስ ሜርሲ ሱዋኒራ /Mrs. Mercy Thuanira/ በበኩላቸው ተቋማቸው ከሚሠራባቸው መስኮች መካከል አንዱ የሕፃናትና ሴቶች ምግብ ዋስትና  መሆኑን ጠቅሰው እንሰት ከኢትዮጵያ አልፎ የምሥራቅ አፍሪካ ብሎም የአፍሪካ የምግብ ችግር መፍቻ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በነበራቸው የመስክ ምልከታ የእንሰት አዘገጃጀት በዋናነት የሴቶችን ከፍተኛ ጉልበትና ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን በተግባር መገንዘባቸውንና ዩኒቨርሲቲው ከዚህ አንጻር የሠራቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራዎች ችግሩን የሚቀርፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንሰት ድርቅን የሚቋቋምና በአነስተኛ ቦታ ብዙ ምርት መስጠት የሚችል ከመሆኑ አንጻር የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራን የሚደግፍ ተክል እንደመሆኑ ተክሉን ኬንያን ጨምሮ ሴቶችን ባሳተፈ መልኩ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ለማስተዋወቅ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራዎች ባሻገር የማኅበረሰቡን አኗኗር የሚያሻሽሉ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚፈቱ ምርምሮችንና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ በእንሰት ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት መታሰቡ የሚበረታታ ተግባር መሆኑንና የታሰበው ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆንና የታለመለትን ግብ እንዲመታ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ይወጣል ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት