የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክቶሬት 10ውን ዓመታዊ የምርምር ግምገማ ዎርክሾፕ ከጥር 19 -20/2015 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የምርምር ሥራ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ዋና ተግባር እንደመሆኑ በሁሉም ትምህርት መስኮች የሚሠለጥኑ ተማሪዎች በምርምር ሥራ የተቃኙና የበቁ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው በድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮችና በምርምር ሥራ ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዓለማየሁ አክለውም እንደእንሰት ፕሮጀክት ሁሉ የተቋሙ የምርምር ሥራዎች በማኅበረሰብ ላይ ተጨባጭና አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳርፉ የምርምር ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠልና መማር ማስተማሩንም ምርምር ተኮር በማድረግ በትኩረት እንዲሠራ በአፅንዖት አሳስበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዎርክሾፑ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በጀት ተመድቦ ሲሠሩ የነበሩ የተጠናቀቁ ምርምሮች ውጤቶች ይፋ የሚደረጉበትና በሂደት ላይ ያሉ ምርምሮች የሚገመገሙበት መሆኑን ገልጸው የግምገማ መድረኩ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለሰፊው ማኅበረሰብ ከማስተዋወቅ ባሻገር የተመደበው በጀትና የተገኘው ውጤት መመጣጠኑን ለማየት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ የሚሠሩ ምርምሮች በዋናነት የማኅበረሰቡን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚችሉ መሆን አለባቸው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ለዚህም በእንሰት ፕሮጀክት የተገኘው አመርቂ ውጤት ጥሩ ማሳያ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የምርምር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በበኩላቸው የግምገማ መድረኩ አጠቃላይ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የሚገመገሙበትና በየዓመቱ የሚካሄድ መርሃ ግብር መሆኑን ጠቅሰው የተጠናቀቁና በሂደት ላይ ያሉ ምርምሮች ያሉበትን ደረጃ ለመለየት መድረኩ ይረዳል ብለዋል፡፡ በጋራ መድረክ 4 የተመረጡ 3 የተጠናቀቁና 1 በሂደት ላይ ያለ ምርምር መቅረባቸውንና ሌሎች የምርምር ሥራዎች ግምገማ በየካምፓሶች የሚቀጥል መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ ከምርምር ሥራ አቅራቢዎች አንዱ በመሆን አይሲቲን በመጠቀም የእንግሊዝኛን ቋንቋ ማስተማርን ማሻሻልን ተተኳሪ በማድረግ የተከናወነውን የምርምር ፕሮጀክት ውጤት አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ አክለውም በፕሮጀክቱ ትግበራ ሂደት በአርባ ምንጭና ሳውላ ከተሞች የሚገኙ የአርባ ምንጭ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ እና የሳውላ 2 ደረጃና መሠናዶ ት/ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን የአይሲቲና መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም እንዲሁም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክሂሎት ሥልጠና ተሰጥቷቸው ቋንቋውን በአይሲቲ ታግዘው እንዲያስተምሩ የተደረገ ሲሆን በዚህም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ሂደትም ከፍተኛ የሆነ የኮምፒውተር ዕጥረት ያለባቸው የአርባ ምንጭ 2 ደረጃና መሠናዶት ት/ቤት 17 እና የሳውላ 2 ደረጃና መሠናዶ ት/ቤት 8 የኮርአይ7 ዘመናዊ ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ድጋፍ ማግኘታቸውንም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ የተገኘው ውጤት እንግሊዝኛ ቋንቋን በአይሲቲ ታግዞ በተሻለ ሁኔታ ለማስተማር የሚያስችል መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም ከፕሮጀክቱ መጠናቀቅ በኋላ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከፕሮጀክቱ የተወሰዱ ልምዶች ቀጣይነታቸው አሳሳቢ ስለሆነ መንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ ተጨማሪ አጋዥ ፕሮጀክቶችን በማፈላለግ ተደራሽነቱን ለማስፋት ቢሠራ ፋይዳው ለሀገር ጉልህ መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡  

በግብርና ኮሌጅ የዕጽዋት ሳይንስ መ/ርና ተመራማሪ ዶ/ር ደግፌ አሰፋ መጤ ተባይ የሚቋቋሙ የበቆሎ ዝርያዎችን በመምረጥና ለማኅበረሰቡ በማስተዋወቅ ላይ የምርምር ሥራቸው ማተኮሩን ገልጸዋል፡፡ ተመራማሪው በቆላማ አከባቢዎች በቆሎ ለምግብነት አገልግሎት በስፋት እንደሚውል ጠቁመው ከዓለም አቀፍ የቆላ ግብርና ኢንስቲትዩት/International Tropical Agriculture Institute/ 32 የተሻሻሉ ዝርያዎችንና አንድ ሀገር በቀል ዝርያ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ ተባዮችን የሚቋቋሙ የበቆሎ ዝርያዎችን ለመለየት ባካሄዱት ጥናት 5 የተባይ መቋቋም ችሎታና ምርታማ ዝርያዎች መለየታቸውን እንዲሁም በጥናቱ የተካተተው ሀገር በቀል ዝርያ በ28% የምርት መቀነስ ውጤት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡  

“Improving the Quality of Teaching English Language through ICT Tools: Arba Minch, Sawla, and Community Secondary Schools in Focus” በዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም፣ “Evaluation of the Performance of Maize Hybrids for Fall Army Worm (spodopterafrugiperda) Resistance under Natural Infestation in the lowlands of Gamo Zone, Southern Ethiopia” በዶ/ር ደግፌ አሰፈ፣ “Assessment of Quality of Care Provided to Adults with Type 2 Diabetes Mellitus at Public Hospitals in Gamo Zone, Southern Ethiopia: Facility Based Cross-Sectional Study” በዶ/ር መንዴ መንሳ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮረ በሂደት ላይ ያለ ጥናት በዶ/ር ሰኢድ አሕመድ በዕለቱ የጋራ መድረክ ላይ የቀረቡ ምርምሮች ናቸው፡፡ በጠቅላላው 120 የምርምር ሥራዎች የሚገመገሙ ሲሆን ቀሪ የምርምር ሥራዎች በየካምፓሶች እንዲገመገሙ ተደርጓል፡፡

በመርሃ ግብሩ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ፣ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራን፣ የ3 ዲግሪ ተማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት