የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድርጅቱና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሰባት ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች በተገኙበት ጥር 20/2015 ዓ/ም ዓመታዊ ጉባዔውን በአርባ ምንጭ ፓራዳይዝ ሎጅ አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ግርማ እንደገለፁት  ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመንገድ ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የባለሙያ ዕጥረት ያለባት ሀገር በመሆኗ ድርጅታቸው ችግሩን ለመቅረፍ ከሰባት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር በመሥራት በሰባት የተለያዩ የምኅንድስና ዘርፎች በ“Structural”፣ “Geotechnical”፣ “Road & Transport”፣ “Hydraulic”፣ “Construction Technology & Management”፣ “Environmental” ምኅንድስና እና  “Hydrology” በባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ብቻ ከ2011 እ.አ.አ ጀምሮ በድኅረ ምረቃ መርሃ ግብር የዘርፉን ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም የፕሮግራሙ ዓላማ በግንባታው ዘርፍ በተለይ በመንገድ ላይ የሚሠሩ የምኅንድስና ባለሙያዎችን አቅምና ዕውቀት ለማሳደግና የግንባታ ወጪን ለመቀነስ፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የጥራትና ብቃት ያላቸው መሐንዲሶችን ዕጥረት ችግር ለመቅረፍ፣ የምርምር አቅምን ለማጎልበት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነው ብለዋል::

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ መድረኩ የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ሂደት ከመገምገም ባሻገር ከሚቀርቡ ጥናታዊ ፅሑፎች፣ ሪፖርቶችና ሠነዶች በቀላሉ የማይገኘውና የማይገዛው ልምድ፣ ዕይታ እና ዕውቀት የሚጋሩበት፣ እርስ በእርስ የሚማማሩበትና ከችግሮች የተቀመሩ የተለያዩ መፍትሄዎች የሚመነጩበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሥልጠና ፕሮግራሙን ሲጀምር በተለይ በሲቪል ምኅንድስና ዘርፍ በሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የሚስተዋለውን የተማረ የሰው ኃይል ዕጥረት መቀነስ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ዓለማየሁ  ከ2005 ዓ/ም እስከ 2011 ዓ.ም በተደረገ ጥረት ሰባት ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶችን በመጠቀም በሺዎች የሚቆጠሩ የዘርፉን ባለሙያዎች በማፍራት ለሀገሪቱ የዘርፉ ሰው ኃይል ፍላጎት መሟላት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው እ.አ.አ በ2013 የተቋቋመው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር/ERA/ ፕሮጀክት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመንገዶች ግንባታ አቅም ማሻሻያ ላይ በትኩረት እየሠራ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው ድርጅቱ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ባለው የትብብር ሥራ ለተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉነህ ኢንስቲትዩቱ በ“CIVIL Engineering” ትምህርት ፕሮግራም የ3 ዲግሪ መርሃ ግብር ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀው ኢንስቲትዩቱ ከድርጅቱ ጋር  የትብብር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በፕሮግራሙ የሀዋሳ፣ አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ መቐለ፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮችና ተወካዮች ርፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ኢንጂነር እህትአበዝ ንጉሤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በጥናትና ምርምር ዙሪያ ስለሚሠራቸው ጉዳዮች ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት