የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስነትምህርትና ስነባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ለዩኒቨርሲቲው ተደራሽ በሆኑ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ ት/ቤቶች የትምህርት ስኬቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ የትምህርቱ ዘርፍ ባላድርሻዎች ምክክር እና የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ታላቅ የምርምር ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ጥር 20/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ትምህርት ለሀገር ግንባታ ያለውን ትልቅ ሚና እንዲጫወት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና ብቁ ዜጋን ማፍራት አማራጭ የሌለው ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ የ2014 ዓ/ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ውጤት እጅግ አሳዛኝና  አስደንጋጭ ክስተት ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ይህም የሀገራችንና በየደረጃው ያለው ማኅበረሰብ ትልቅ ኪሣራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን በሳይንሳዊ መንገድ ለይቶና ተንትኖ በመፍትሄዎች ላይ መሥራትና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ማቅረብ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠበቅ ዋና ተግባር በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡

የምርምር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በትምህርት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ምርምሮች ሲቀርቡ ዳይሬክቶሬታቸው በቀዳሚነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚደግፍ ገልጸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በልዩ ቁርጠኝነት መሥራት በሚገባን ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ተዘጋጅቶ ይፋ በተደረገው አዲሱ ታላቅ የምርምር ፕሮጀክትና በቀጣይነትም በዚህ ዘርፍ በሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ላይ ዳይሬክቶሬታቸው ትኩረት እንደሚያደርግ ዶ/ር ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የስነትምህርትና ስነባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ ትምህርት ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያስተሳስርና በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ንቁ ተሳትፎ የሚኖራቸውን ዜጎች ለማፍራት የሚረዳ መሣሪያ እንደመሆኑ የትምህርት አፈጻጸምን ከማሻሻል፣ ጥራቱን ከማስጠበቅና ውስጣዊ ብቃትን ከማሳደግ አኳያ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ሀገራዊው የ12 ክፍል ማጠቃላያ ፈተና ውጤት አመላካች ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዲኑ ገለጻ ሀገራችንንና የትምህርት ሥርዓቱን ለመታደግ ከመቸውም ጊዜ በላይ በጋራ፣ በቅንጅትና በትኩረት መሠራት ያለበት ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው ባለድርሻ አካላት ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም ትውልድንና ሀገርን ለማዳን ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል፡፡

በዕለቱ በትምህርት ተግዳሮቶች ዙሪያ ባቀረቡት የምርምር ግኝት ውጤት የትምህርት አመራሩ ሚና ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱን የገለጹት የት/ቤቱ መምህርና ተመራማሪ ረ/ፕ ሰለሞን ሳጶ መድረኩ በምርምር የተገኙ ውጤቶችን ወደታች በማውረድ ለመተግበር የሚያስችሉ ገንቢ የሃሳብ ግብዓቶችን ያገኙበት ሲሆን የተሠሩ ምርምሮችን መደርደሪያ ላይ ከማስቀመጥ ባለፈ በተግባር ላይ በማዋል ለለውጥ መሥራት ተጋቢና ወቅታዊም ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ግኝቶች ላይ መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን፣ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ በሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላሉ ትምህርት ቤቶች እየተደረጉ የሚገኙ ድጋፎችንና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የስነትምህርትና ስነባህሪ ሳይንስ ት/ቤት የምርምር አስተባባሪና ተመራማሪ ዶ/ር ቤታ ጸማቶ የአዲሱ የተማሪዎች ውጤት ማሻሻያ ታላቅ የምርምር ፕሮጀክት ዋና ተመራማሪ መሆናቸውን ጠቅሰው ካለፉ ዓመታት የተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማነስ በመነሳት “Revitalizing Students’ Academic Success in Government Secondary School of Town Administrations over Arba Minch University Catchment Areas” በሚል ርዕስ የፕሮጀክቱን ጥናት ንድፍ ማዘጋጀታቸውን ገልጸው ፕሮጀክቱ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የተማሪዎች የትምህርት ስኬት ማሳለጫ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ 1.75 (አንድ ነጥብ ሰባት አምስት) ሚሊየን ብር በጀት እንዳለው፣ በ3 ዓመታትና 3 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ፣ በዩኒቨርሲቲው ተደራሽ በሆኑ 3 ዞኖችና በ2 ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ ስምንት የ2 ደረጃ ት/ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ ዋና ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ቤታ አክለው እንደተናገሩትም የተቀረጸው ፕሮጀክት ተማሪዎች ራዕይ እንዲኖራቸው፣ በትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶች እንዲሟሉና የትምህርት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ ያስችላል፡፡

ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ችግሩን ለይቶ ለመፍትሄ ላይ እየሠራ መሆኑ ወሳኝና ወቅታዊ ጉዳይ ሲሆን እኛም እንደትምህርት አመራርና ባለድርሻ አካላት የትምህርቱን ዘርፍ ችግር በመፍታትና የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የሀገራችንን መጪ ዕጣ ፋንታ ከወዲሁ ለማስተካከል የምጠበቅብንን ሚና በጉልህ ለመጫወት፣ የሚቀርቡ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለመደገፍና ለትምህርት ስኬታማነቱ ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ለስኬቱ እንተጋለን ብለዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ አክለውም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ለሁሉም ደረጃዎች መሠረት ስለሆነ በአዳዲስ ፕሮጀክቶችና በፖሊሲ ደረጃም በትኩረት መሥራት ከተቻለ ችግሩን ከስሩ ለማጥፋት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ 3 ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ያለቁ የምርምር ውጤቶችና 1 የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች አፈጻጸምን የተመለከተ ሠነድ ገለጻዎች ቀርበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ምሁር በዶ/ር መለሰ መንገሻ የተዘጋጀ የቅድመ መደበኛ እስከ 4ኛ ክፍል የሚያገለግል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፍኖተ ንባብ አጋዥ መጽሐፍ ድጋፍም ከዞኖቹና ልዩ ወረዳዎቹ ለመጡ ተወካዮች ተበርክቷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ከጋሞ፣ ጎፋና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ከደራሼና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የትምህርት አመራሮችና  ባለድርሻ አካላት፣ ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮችና ዲኖች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡  

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት