Print

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የስነሕንፃና ከተማ ፕላን ፋከልቲ ሕንድ ሀገር ከሚገኘው ሂንዱስታን የቴክኖሎጂና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የምርምር ዓውደ ጥናት ከጥር 22-23/2015 ዓ/ም በበይነመረብ አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዪኒቨርሲቲ የምርምር ኤክስኪዩቲቨ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንደገለፁት ዓውደ ጥናቱ ውጭ ሀገር ከሚገኝ ተቋም ጋር በትብብር ለመጀመሪያ ጊዜ በበይነ መረብ የተደረገ እንደመሆኑ የተሻሉ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ከመጋራት አንፃር ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች ትምህርት ተቋማት በተለየ መልኩ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምር የማካሄድ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተስፋዬ ከዚህ አንፃር ዩኒቨርሲቲው ለመስኩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ኢንስቲትዩቱ ከሂንዱስታን የቴክኖሎጂና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር አብሮ ለመሥራት ከአንድ ዓመት በፊት ባደረገው ስምምነት መሠረት የጋራ የበይነ መረብ የምርምር ዓውደ ጥናቱ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉነህ ዓውደ ጥናቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተጀመረውን ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር በተቋማቱ ለሚገኙ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች በእጅጉ የሚጠቅም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የስነሕንፃና ከተማ ፕላን ፋከልቲ ዲን አቶ ገረመው ገ/ማርያም በበኩላቸው እንደተናገሩት ከሂንዱስታን የቴክኖሎጂና ሳይንስ ኢንስቲትየት ጋር በጋራ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለመክፈት፣ ምርምሮችን ለማካሄድ እና የመምህራንና ተማሪዎች ልውውጥ ለማድረግ በተደረገው ስምምነት መሠረት የትብብር ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በትብብር የተዘጋጀው የበይነ መረብ ዓውደ ጥናቱ የዚሁ ስምምነት አካል ሲሆን በመድረኩ ከሁለቱም ወገን ከኪነሕንጻና ከተማ ፕላን ጋር የተገናኙ 30 የምርምር ሥራዎች ቀርበው የፊት ለፊትና የበይነ መረብ ውይይት መደረጉን ዲኑ አክለው ገልጸዋል፡፡

“Planning and Design Assistance for Cluster፡ Governing Growth Aspect of Urban Center's Towards Sustainable Development in Southern Ethiopia”፣ “Relationship between Sustainable Housing Practices from Traditional Indian Culture and Environmental Sustainability” እና “Fashion Campus Design” የሚሉት ከቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉ ሲሆን የምርምር ሥራዎቻቸውን ላቀረቡና ከ1-3 ደረጃ ላገኙ ምርምር አቅራቢዎች ሽልማት እንዲሁም ለሁሉም ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡   

የብሩህ ተስፋ ማዕክል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት