የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ለ2015 ዓ/ም አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች የካቲት 30/2015 ዓ/ም የእንኳን ደኅና መጣችሁ መርሃ ግብር አዘጋጅተዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ሴቶች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጾታዊ ችግሮች እንዳይገጥሟቸው አስቀድሞ ለመከላከልና ቢከሰቱም አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ የሚያስችል የማማከር አገልግሎት፣ የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ድጋፍና የተለያዩ ሥልጠናዎች በዳይሬክቶሬቱ ይሰጣሉ ብለዋል፡፡ ሴት ተማሪዎች ብቁና ውጤታማ እንዲሁም ከወንዶች እኩል ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ወ/ሮ አዳነች እልፍነህ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈው የቢሮውን አደረጃጀት፣ የሥራ ክፍሉን ዋና ዋና ተግባራት፣ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የሚጠበቁ ተግባራት እና አዲስ ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሊገጥሟቸው በሚችሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን ሥነ ምግባር የሕይወት መመሪያ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎች የሃይማኖት፣ የባህልና የአመለካከት ልዩነት አቻችለው የመጡበትን ዓላማ በስኬት ማጣናቀቅ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የዩኒቨርሲቲውን የዲሲፕሊን መመሪያ ዐውቀው መብታቸውን በመጠቀምና ግዴታቸውን በአግባቡ በመወጣት የመልካም ሥነ ምግባር ባለቤት መሆን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ በተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ስለ ኅብረቱ አደረጃጀትና ተግባራት ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች መነሳሳትን እንዲፈጥር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት