በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል በባዮቴክኖሎጂ ትምህርት ፕሮግራም ላለፉት አምስት ዓመታት የ3 ዲግሪ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው ዕጩ ዶ/ር ብርሃኑ ገመዳ የምርምር ሥራውን መጋቢት 22/2015 ዓ/ም የውስጥና የውጪ ገምጋሚዎች በተገኙበት አቅርቦ ተገምግሟል፡፡ የመመረቂያ ጽሑፉም አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ፎቶውን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

‹‹Characterization of Bacteria Causing Ensete [Ensete ventricosum (Welm.) Cheesman] Wilt Disease and its Management Strategies in Gamo Highlands of Ethiopia›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፉን ያከናወነው ዕጩ ዶ/ር ብርሃኑ ገመዳ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደበት በጋሞ ዞን በጨንቻ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትሏል፡፡

ዕጩ ዶ/ር ብርሃኑ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ ላቦራቶሪ ቴክኒሻንነት በዲፕሎማ የተመረቁ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ የትምህርት መሰክ አግኝቷል፡፡ ዕጩ ዶ/ር ብርሃኑ በመምህርነትና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች በዩኒቨርሲቲው ሲያገለግል ቆይቶ የ3 ዲግሪ ትምህርቱን በባዮ-ቴክኖሎጂ ትምህርት ፕሮግራም ተከታትሎ ለማጠናቀቅ ችሏል፡፡

በግምገማ መርሃ ግብሩ የውስጥና የውጪ ገምጋሚዎችን ጨምሮ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የዘርፉ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ታድመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት