አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም እና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን የእንሰት መፋቂያ፣ መቁረጫ፣ መፍጫና መጭመቂያ ማዕከል በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ሆሎኦ ቀበሌ አቋቁሟል፡፡ በዚህም የአካባቢው እንሰት አብቃይ ሴት አርሶ አደሮች እንሰት ወደ ማዕከሉ በማምጣት በቴክኖሎጂው በመገልገል ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የእንሰት ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ዩኒቨርሲቲው የእንሰት ተክል አመራረትና ማብላላት ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ምርምሮችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ለእንሰት አብቃይ አርሶ አደሮች ሲያስተዋውቅና ሲያላምድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አዲሱ አክለውም በዩኒቨርሲቲው የበለጸጉት ቴክኖሎጂዎች፡- እንሰት በመፋቅ፣ በማብላላትና ሌሎች ሂደቶች ላይ የሚስተዋለውን አድካሚ የጉልበት ሥራና ጊዜ በእጅጉ የሚቀንሱ ከመሆናቸውም ባሻገር ከ24 እስከ 45 በመቶ   የነበረውን የምርት ብክነት ሙሉ በሙሉ የሚያስቀሩ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ በእንሰት መፋቅ ሂደት ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም ማሽኖች የያዘ በመሆኑ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ማዕከል እንደሚያደርገው ዶ/ር አዲሱ ገልጸዋል፡፡

በማዕከሉ ከ1200 በላይ ሴት አርሶ አደሮች እየተጠቀሙ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር አዲሱ በቅርቡም በወላይታ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ ክርስቲያን ኤይድ በተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት የተገነቡ ሁለት ማዕከላት ሥራ ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም በጋሞ ዞን ጨንቻ፣ ገረሴና ዲታ ወረዳዎች ላይ መሰል ማዕከላትን የመመሥረት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቴክኖሎጂዎቹ ምርትን ከማሳደግና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ያላቸውን ፋይዳ በመገንዘብ ለአርሶ አደሩ በስፋት ለማዳረስ በትብብር እንዲሠራ ጠቃሚ ይሆናል ሲሉ የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡  

በማዕከሉ ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል ወ/ሮ ገበያነሽ አልታ በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ በመንደራቸው ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ አገልግሎቱን እያገኙ መሆናቸውንና በባህላዊ መንገድ ቀናት ይፈጅ የነበረው የመፋቅ፣ የመቆራረጥ፣ የመፍጨትና የመጭመቅ ሂደት ቀርቶ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ሥራቸውን እንደሚያጠናቅቁ ተናግረዋል፡፡ በማዕከሉ የሚገኙ ማሽኖች ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል በመሆናቸው በባህላዊ መንገድ ሲሠሩ የሚደርስባቸውን ድካምና ልፋት ከማስቀረቱም ባሻገር ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን ወ/ሮ ገበያነሽ ጠቁመዋል፡፡ በማዕከሉ በአካባቢው ያሉ በርካታ አርሶ አደሮች እየተጠቀሙ እንዳሉ ገልጸው በርቀት ላይ ባሉ ሌሎች አካባቢዎችም መሰል ማዕከላት ቢቋቋሙ በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተጠቃሚዋ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 

 በቴክኖሎጂዎቹ አጠቃቀም ዙሪያ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው ሥልጠና መውሰዳቸውን የሚናገሩት ሌላኛዋ እንሰት አብቃይ አርሶ አደር ወ/ሮ ብርቱኳን ቴማ በበኩላቸው በሥልጠናው መሠረት ቆጮን በፕላስቲክ ማብላያ በማብላላት ጥራቱን የጠበቀ ምርት ያለምንም ብክነት ማግኘት መቻላቸውን ገልጸው ማዕከሉ በሴቶች ላይ የነበረውን ከፍተኛ የሥራ ጫና አስቀርቷል ብለዋል፡፡

የእንሰት አመራረት ሂደቱን ማሻሻልና ማዘመን መቻል የእናቶችን ድካም በእጅጉ ከመቀነሱና ጊዜያቸውን ከመቆጠቡ በላይ ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የበለጸጉ የእንሰት ቴክኖሎጂዎችን በሁሉም እንሰት አብቃይ አካባቢዎች ለማዳረስ የሚመለከታቸው አካለት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር የቆጮ ዱቄትን ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ የብራንዲንግና የቆጮን የሥነ-ምግብ ይዘት በጥልቀት የማጥናት ሥራዎች አውሮፓና አሜሪካ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየተሠራ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ሥራዎች በቅርቡ ሲጠናቀቁ የቆጮ ዱቄት ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ እንደሚቀርብም የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት