የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብዝኃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል የእንሰት አጠውልግ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስና ከበሽታው የጸዱ የእንሰት ዝርያዎችን አባዝቶ የማሰራጨት ተግባራትን የሚያከናውን ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ቀርጾ በጋሞና ጎፋ ዞኖች በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የብዝኃ ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሽቴ ጋተው ዕጽዋትና እንስሳት ብዝኃ ሕይወት፣ መድኃኒትነት ባላቸው የዕጽዋት ዝርያዎች ላይ፣ በተረሱ ነገር ግን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ዕጽዋት ላይ፣ በውኃ ሥነ ምኅዳርና ፓርኮች ላይ ምርምርና ጥበቃ ማካሄድ የማዕከሉ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ በዶርዜና በአርባ ምንጭ የዕጽዋት ምርምርና ጥበቃ ሳይቶች ያሉት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ በዚህም እንሰትን ጨምሮ በርካታ ሀገር በቀል ዕጽዋትን በማሰባሰብ ጥበቃ ብሎም ምርምር እያደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡  

ማዕከሉ በየዓመቱ ከ10 ያላነሱ የምርምር ሥራዎችን እንደሚያከናውን የገለጹት ዶ/ር ሽቴ ከነዚህ የምርምር ሥራዎች መካከል ከእንሰት አጠውልግ በሽታ የጸዳ የእንሰት ምርት እንዲኖር ለማስቻል ተግባራዊ የተደረገው ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡ "Reducing Bacterial Wilt Epidemics in Enset Farms of Gamo and Gofa Zones" የተሰኘው ፕሮጀክት ለአራት ዓመታት የሚቆይና ጥበቃ፣ ምርምር እንዲሁም ማኅበረሰብን ማገዝ የሚለውን የማዕከሉን ተልዕኮ ያሟላ ሆኖ ከ1.1 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ለማስፈፀሚያው መመደቡን ዶ/ር ሽቴ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የሆርቲካልቸር መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ የእንሰት አጠውልግ በሽታ ከእንሰት የሚገኘውን ምርት የሚቀንስ ዋነኛ ችግር ሲሆን ከዚህ ቀደም በበሽታው የተደረጉ ጥናቶች በውስን ቦታዎች ላይ የተከናወኑ መሆናቸው እንዲሁም በመጀመሪያው ጥናት ያልተመለሱ ጥያቄዎች በመኖራቸው የምርምር ፕሮጀክቱን መቅረጽ አስፈልጓል ብለዋል፡፡ የምርምር ሥራው በጋሞና ጎፋ ዞኖች በሚገኙ ዲታ፣ ጨንቻ፣ ካምባ፣ ቆጎታና ገዜ ጎፋ ወረዳዎች እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑን የገለጹት ዋና ተመራማሪው የበሽታውን ስርጭት ማጥናት፣ አባባሽ ምክንያቶችን መለየት፣ የምርምር ውጤቶችን መሠረት በማድረግ በበሽታው ምልክቶች፣ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ዙሪያ ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ መፍጠር፣ ከበሽታው የጸዱ ችግኞችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አባዝቶ ማሰራጨት ዋነኛ የፕሮጀክቱ ግቦች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በ2013 ዓ/ም የተጀመረ ሲሆን ሦስት የ2 ዲግሪ ተማሪዎችም ለፕሮጀክቱ ተጨማሪ ግብዓት ሊሆን የሚችል ምርምር እያከናወኑ መሆናቸውን ዶ/ር ሳቡራ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዋና ተመራማሪው እስካ አሁን ባለው የፕሮጀክቱ ሂደት አስፈላጊ መረጃዎች የተሰበሰቡ ሲሆን ቀሪ ሥራዎች ሲጠናቀቁ  የምርምር ውጤቱ ይፋ ይሆናል፡፡ ዶ/ር ሳቡራ በፕሮጀክቱ ከ45 ሺህ በላይ ከበሽታ የጸዱና የተለያየ ዝርያ ያላቸው የእንሰት ችግኞችን አባዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ የታቀደ ሲሆን እስካ አሁን ባለው አፈፃፀም ከ21 ሺህ በላይ ችግኖችን በካምባና ገዜ ጎፋ ወረዳዎች ለሚገኙ ከ400 በላይ አርሶ አደሮች ማዳረስ ተችሏል ብለዋል፡፡ ይህም የበሽታውን ስርጭት ከመግታት አንፃር ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን ዋና ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡ ዋና ተመራማሪው እንደጠቆሙት በፕሮጀክቱ ሥራ የአካባቢው አርሶ አደሮች ደስተኛ ሲሆኑ ፕሮጀክቱ የአርሶ አደሩን ህልውና ከማስቀጠል እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡

የምርምር ማዕከሉ ከዚህም በተጨማሪ በአርባ ምንጭ በሚገኘው ሰርቶ ማሳያና በዶርዜ እንስት ፓርክ በርካታ የእንሰት፣ የሽፈራው፣ የቅመማ ቅመም፣ የመድኃኒት፣ የቅባት ሰብሎችንና ሌሎች በመጥፋት ያሉ ሀገር በቀል የዕጽዋት ዝርያዎችን ከተለያዩ ስፍራዎች በማሰባሰብ የመጠበቅ እንዲሁም በዕጽዋቱ ላይ ምርምሮችን እያከናወነ ሲሆን በቀጣይ በመጥፋት ላይ የሚገኙ የዕጽዋት ዝርያዎችን አባዝቶ የማሰራጨት ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን የማዕከሉ ተመራማሪና የአርባ ምንጭ ሰርቶ ማሳያ አስተባባሪ አቶ አታላይ አዘነ ገልጸዋል፡፡ በአርባ ምንጭ በሚገኘው ሰርቶ ማሳያ ብቻ ከ67 በላይ የዕጽዋት ዝርያዎች ተሰብስበው ጥበቃ እየተደረገላቸው የሚገኝ ሲሆን በተወሰኑት ላይም ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት