Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ጉድ/ማስ/ጽ/ቤት ከጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር በዳራማሎ ወረዳ ለዋጫ ከተማ ወጣት አደረጃጀት፣ ኢንተርፕራይዝ አካላትና ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለተወጣጡ አካላት በአመራርነት፣ በሥራ ፈጠራ አመለካከትና የስኬታማ ሥራ ፈጣሪዎች መለያ ባህሪያት ዙሪያ ያተኮረ ሥልጠና ሚያዝያ 03/2015 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሥራን ከመፈለግ  ይልቅ ሥራን ፈጣሪ ለማፍራት ታልሞ እየተሠራ ነው ያሉት የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ርት አስቴር ሰይፉ  የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት በተቋሙ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ የወጣት አደረጃጀቱ፣ የኢንተርፕራይዝ አካላቱና የአመራሮቹ የዕውቀት ክፍተት እንዲሞላ በመሰል ሥልጠናዎች መታገዛቸው ፋይዳው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ወጣቶችና  ስፖርት መምሪያ ም/ኃላፊና የወጣት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ማርቆስ በሀገራችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም የሚፈለገውን ደረጃ እንዳልደረሰ ገልጸው ሁሉ አቀፍ ሥልጠናዎችን አጠናክሮ በመስጠት በሁሉም አከባቢዎች እኩል ተነሳሽነትን በመፍጠር ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማገዝ ታልሞ ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ እንደ ኃላፊው በተጨማሪም ወጣቱ ወደ ሥራ ሲገባ የአመራር ማነቆ በመኖሩ በመሪነት ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት ተገቢውን ግልጋሎት ለመስጠት እንዲቻል ሥልጠናው አመራሩንም ለማብቃት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ በቀጣይም  ወጣቱ ራሱን በማዘጋጀትና በመደራጀት አዋጭ ሥራ መፍጠር ከቻለ ባለድርሻ አካላት ወደ ሥራ ለማስገባት በባለቤትነት ስሜት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የዳራማሎ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ም/ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ  ኃላፊ አቶ ገዘኸኝ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የተቃና አስተሳሰብ ያለውና ምክንያታዊ ወጣትን ማፍራት ለሀገር ዕድገት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ማንኛውም ሰው እራሱን ለመለወጥ በአስተሳሰብና በአመለካከት ራሱን ማነጽ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሠልጣኞች የወሰዱት ሥልጠና ሕይወታቸውን ለመቀየር የሚረዳና ሥራና ሥራ ፈላጊን የሚያገኛኝ ድልድይ በመሆኑ ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በመተግበር ለለውጥ እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡ በሥራ ክፍላቸውም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸው ሥልጠናውን ላመቻቹ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ መ/ር ዋጋው ደምለው በአመላካከትና የስኬታማ ሥራ ፈጣሪዎች መለያ ባህሪያት ላይ የሥልጠናው ይዘት ማተኮሩን ገልጸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኘውን ሥራ አጥነት ለመቀነስ ወጣቶች ያላቸውን አቅም እንዲሁም በአከባቢያቸው ላይ ያለውን ዕምቅ ሀብትና በኅብረተሰቡ ዘንድ ያልተሟላ ፍላጎትን በመለየት ወደ ሥራ እንዲሠማሩ በማገዝ የሀገራችንን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ትውልድ ለማፍጠር  ሥልጠናው ይረዳል ብለዋል፡፡ እንደ አሠልጣኙ መሰል ሥልጠናዎች ፋይዳቸው የላቀ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለሥልጠናው አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ምን ዓይነት አመራርነት እንደሚያስፈልግ ለማሳየት የሞከሩት ሌላኛው አሠልጣኝ የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህር ተዛና በቀለ አመራርነት ቀላል ቢመስልም ውስብስብና ከባድ እንደሆነ ገልጸው መሪዎች በዕውቀትና በብቃት የመሪነትን ስብዕና መላበስ  እንሚገባቸው አመላክተዋል፡፡ሥልጠናው በመሪዎችም ዘንድ የሚስተዋሉ የአመራሪነት ክፍተቶችን ለመሙላት ታቅዶ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በቀጣይ በወረዳ ብቻ ባሉ አመራሮች ሳይወሰን በየደረጃው ላሉ አመራሮች ቢሰጥ  ለሀገር መሪነትና ለተቋም ጥራት ያላቸውን ሚና ማሳደግ እንደሚቻል  አሠልጣኙ ጠቁመዋል፡፡

ሠልጣኞችም  በሰጡት አስተያየት ከስንፍና በመላቀቅ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያነቃና  ሥራን በመፍጠር ለሌሎች አርአያ መሆን የሚያስችል ዕውቀት እንዳገኙ ገልጸው በአመራርነት ሚና ላይ ያሉ የዕውቀት ክፍተቶችን በመሙላት ብቁ ለመሆን እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ ቀጣይነት ያላቸው ሥልጠናዎችን በመስጠት የማብቃት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም  ሠልጣኞቹ አሳስበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት