Print

የተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና አሠጣጥ እና የሪሜዲያል ተማሪዎች የማስተማር ሂደትን አስመልክቶ የተከናወኑ ተግባራት ያሉበት ሁኔታ እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ዲኖች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች፣ ከየትምህርት ክፍሉ የተወጣጡ ተማሪዎችና የተማሪዎች ኅብረት ተወካዮች በተገኙበት ግምገማዊ የውይይት መድረክ ሚያዝያ 11/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የውይይት መድረኩ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገም ከትምህርት ክፍሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን የሚያሳይ ልምድ የሚወሰድበትና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ ከትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ጋር በመቀናጀት ለመውጫ ፈተና ዝግጅት የሚረዳ የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎች ለፈተናው ዝግጁ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ለሪሜዲያል ተማሪዎችም እየተሰጠ ያለውን የትምህርት አሰጣጥ ሂደት አስመልክተው ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ መምህራን ጠንክረው በመሥራት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማስቻልና ድጋፍ በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ሂደቱን በጋራ መገምገም አስፈልጓል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች የጥናት ፕሮግራም አውጥተው ተረጋግተው በማጥናት በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ክትትል፣ ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ በዝግጅት ምዕራፉ ተማሪዎችን ለፈተና ዝግጁ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው በቀጣይም የተስተዋሉ ክፍተቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ የመውጫ ፈተናዎችን በመስጠት ልምድ ካላቸው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የሕግ ትምህርት ቤት ተሞክሮ አንጻር የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ከተማሪዎች ለተነሱ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት