የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሚያዝያ 12/2015 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ቀርቦ ተገምግሟል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ይፍሩ ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት እንደተመለከተው በ2015 በጀት ዓመት በመደበኛና በካፒታል በጀት 1‚855‚724‚400.00 ብር ለዓመቱ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ተመድቦ 83.58 በመቶው ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን የውስጥ ገቢን ከማሳደግ አንጻር 43,931,593 ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡

በ2015 የትምህርት ዘመን በተቋሙ ባሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች በአጠቃላይ 26‚382 ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከተታል ላይ የሚገኙ ሲሆን የ2015 ዓ/ም አዲስ ገቢ ተማሪዎችን አስመልክቶ በተፈጥሮና ማኅበራዊ ሳይንስ መስኮች 1,648 መደበኛ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ በተጨማሪም በመደበኛ የአቅም ማሻሻያ ፕሮግራም 1‚306 እና መደበኛ ባልሆነ ፕሮግራም 981 በድምሩ 2,287 ተማሪዎች የአቅም ማሻሻያ ትምህርታችውን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡

የመምህራን የማዕረግ እድገትን አስመልክቶ አራት መምህራን የተባባሪ ፕሮፌሰርነት፣ 35 መምህራን ረዳት ፕሮፌሰርነት እና 86 መምህራን ሌክቸረርነት አካዳሚክ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በመምህራን የትምህርት ዕድል በኩል በሀገር ውስጥ 20 የ2ኛ ዲግሪ እና 40 የ3ኛ ዲግሪ እንዲሁም በውጭ ሀገር አንድ የ2ኛ ዲግሪ እና 27 የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷል፡፡

በምርምር ዘርፍ አስከ 3ኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ 600 ነባርና 170 አዳዲስ ምርምሮች እየተከናወኑ ሲሆን በማኅበረሰቡ ችግር ላይ ያተኮሩ ሰባት ግራንድ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ መግባታቸው፣ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ትኩረት መስክ ለሚሠሩ 15 የድኅረ ምረቃ የግል ተማሪዎች የምርምር ገንዘብ ድጋፍ መደረጉና ከውጭ ተቋማት ጋር በትስስር አንድ የምርምር ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱ ተብራርቷል፡፡ በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ አራት የቴክኖለጂ ሽግግር ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን ክርስቲያን ኤይድ የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት በመደበው 3.2 ሚሊየን ብር የእንሰት ቴክኖሎጂዎች ተሠርተው ርክክብ ተካሂዷል፡፡

ለ3‚758 የማኅበረሰብ አባላት ነፃ የሕግ ጥብቅና አገልግሎት መሰጠቱ፣ 8 ችግር ፈቺ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑ፣ የተለያዩ የአካባቢና ደን ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸው፣ በቦረና፣ ካምባ፣ ጎፋና ኮንሶ አካባቢዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት ለድርቅ ለተጋለጡ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉ እንዲሁም ለጋሞ ባይራ ሞዴል አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 25 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ፣ ከ2015-2018 ዓ/ም የመምህራን ደመወዝ ክፍያና የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ጠንካራ አፈጻጸሞች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ት/ቤት በ2014 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 106 ተማሪዎች 31 ተማሪዎች 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ያመጡ ሲሆን አንድ ተማሪ 629 ነጥብ በማምጣት ከክልሉ 2ኛ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በቀጣይ የትምህርት ጥራት፣ አግባባነት፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ፣ የማኅበረሰብ ጉድኝትና የሳይንስ ባህል ግንባታ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን ማሳደግ፣ የተቋማት ትስስርና ተሳትፎ፣ ሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ማሳደግ፣ የትምህርት አመራርና አስተዳደርን ማጠናከር፣ የትምህርት ተቋማዊ አቅምና ብቃት ማጎልበት፣ የትምህርት መሠረተ ልማትን ማሳደግ፣ የሀብት ምንጭና አጠቃቀም ውጤታማነትን ማሳደግ፣ የምርምር እና ፈጠራ ሥራዎች ተደራሽነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ማጣጣምና ማሳደግ ትኩረት የሚሹና በተጠናከረ ሁኔታ ሊሠሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የቅድመ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተና አፈጻጸም፣ የመመረቅ ምጣኔ መረጃ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ዓለም የገቡ ተመራቂ ተማሪዎች፣ በዩኒቨርሲቲውና በአጋር አካላት የሚሠሩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ ከውጭ ሀገር የተገኙ ፈንዶች፣ ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች/ተቋማት/ድርጅቶች ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች በተደራጀ ሁኔታ ሪፖርት ማድረግ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በግምገማ መድረኩ ከካውንስል አባላት የአፈጻጸም ሪፖርቱን መሠረት ያደረጉና ትኩረት ሊደረግባቸው እንዲሁም በሪፖርቱ ሊካተቱ በሚገቡ አፈጻጸሞች ዙሪያ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት