አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሠላም ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ‹‹ሀገር በቀል ዕሴቶችን ለዘላቂ ሠላምና ጠንካራ ሀገራዊ መንግሥት ግንባታ›› በሚል ርዕስ ከሚያዝያ 20-21/2015 ዓ/ም ሀገራዊ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሠላም ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶ/ር የሺመብራት መርሻ ሀገር በቀል ዕሴቶች ላይ የተካሄዱ ምርምሮችና ምርምሮቹን መሠረት አድርገው የተካሄዱት ውይይቶች በጣም ወሳኝና አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸው ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች የተገኙ ግኝቶችንና የመፍትሄ ሃሳቦችን በማሰባሰብና በማቀናጀት ተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንዲሁም በዘርፉ ላይ እየተካሄዱ ያሉ ሌሎች ምርምሮችንም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደር የሺመብራት የባህል ሽምግልና ውጤቶችም በፖሊሲ ተደግፈው መጽደቅ እንዳለባቸው እና እርስ በርስ ያለውን ግጭት ለመፍታት እንዲሁም የትምህርት ሥርዓትን ለማሻሻል መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

አምባሳደሯ አክለውም የሀገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀም ግጭትን መከላከልና ግጭት ከተከሰተ በኋላም የመፍቻ ዘዴዎችን አስመልክቶ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮዎችን አካፍለዋል፡፡ ዕሴቶቻችንን በመጠበቅና በማክበር የባህል አባቶችን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም ወጣቶችን አደራጅቶ በኅብረተሰቡ ዘንድ የቀድሞ የእርስ በርስ ተጋምዶ እንዲኖር መሥራት እንደሚያሻ ገልጸው ይህም የሚሆነው በባህላዊ የአባቶች ምክር እና በሕዝቡ አንድነትና መተሳሰብ ነው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም አምባሳደር የሺመብራት የጋሞ አባቶች የሀገርን ሠላም ለማስጠበቅ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ እየተማረ እንዳለ ጠቁመው የሀገር ሽማግሌዎቹንም አመስግነዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደተናገሩት ሀገራችን የበርካታ ሀገረሰባዊ የግጭት አፈታትና ሠላም የማስፈን ዕሴቶች ባለቤት ብትሆንም በጊዜ ሂደትና በወቅታዊ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ምክንያት ተግዳሮቶች እየገጠሟት ከመሆኑም ባሻገር ለምናከናውናቸው ፈርጀ ብዙ የልማት ተግባሮች ዕሴቶቻችንን ባለመጠቀማችን ሠላማችንንና ልማታችንን ዘላቂ ለማድረግ ችግር ሲገጥም ይስተዋላል ብለዋል፡፡ እነዚህ ሀገረሰብ ዕሴቶች ተቋማዊ አደረጃጀት ተፈጥሮላቸው ቢተገበሩ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዳምጠው ለሰው ልጆች መሠረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ሠላም እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ዕሴቶች ለዘላቂ ሠላምና ለሁለንተናዊ ማኅበረሰባዊ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡    

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ከሁሉም በላይ ሠላም የሰው ልጆች መሠረታዊና ተፈጥሯዊ መብት ሲሆን የሠላም እጦት የግለሰቦችን አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጤናማነት አሉታዊ በሆነ መልኩ በእጅጉ እንደሚጎዳ የገለጹ ሲሆን በአጠቃላይ እንደ ሀገር ከግጭት የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙትን ባህላዊና ሀገር በቀል የችግር መፍቻና የሠላም የማስቀጠያ ሥርዓቶችን በመጠቀም በሕዝቦች መካከል መተማመንን፣ አካታች ሥርዓተ መንግሥት መመሥረትን፣ አስተማማኝ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ለመመሥረት ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተቆጥረው የማያልቁ የተለያዩ ችግር የመፍቻ ባህሎች፣ ልማዶች፣ ወጎችና እምነቶች ያሏት እንደመሆኗ መጠን በባህሎቻችን ውስጥ የሚገኙትን ወርቃማ ሀገር በቀል የችግር መፍቻ ሥርዓቶችን ከተደበቁበት አውጥተን ልንጠቀምባቸውና የራሳችንን ችግር በራሳችን ችግር የማስወገጃ ብልሃት ልንፈታው እንደሚገባ ም/ፕሬዝደንቱ አክለዋል፡፡

በሠላም ሚኒስቴር የግጭት አስተዳደር ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይርጋዓለም መንግሥቱ በበኩላቸው ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶች በሁሉም ሀገሮችና አካባቢዎች ያሉ ሲሆን ሀገር በቀል ዕውቀቶች የማኅበረሰቡን ችግር በመቅረፍ፣ የሀገር ሽማግሌዎችን ተጠቅሞ ዕርቅ በማውረድ፣ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታት፣ ካሳ በመስጠት እና በአጠቃላይ ቂም በቀልን በማስወገድ ደረጃ ሚናቸው የማይተካ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ ይርጋለም በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ወይም ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓቶች በፍርድ ቤትና በምክር ቤት ደረጃ እንዲቋቋሙ እየሠሩ እንዳሉና ከተለያዩ ክልሎች ተሞክሮዎችን መውሰዳቸውን አክለው ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ምሁራን በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ፣ ሌሎች ተቋማትም ክፍተቶችን መሙላትና መደገፍ እንዲችሉና ዕቅዱ  በፖሊሲ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኝ በቀጣይ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ 

አውደ ጥናቱ ሀገር በቀል ዕሴቶችን ከማስቀጠል አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዋና ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው በዕሴቶቹ ላይ በርካታ ጥናቶችን በማድረግና ለውይይት በማቅረብ ማኅበረሰቡ የራሱን ባህል እያከበረ የሚሄድበትን መንገድ እንዲሁም ባህልን ከባህል ጋር በማገናኘት እና ተሞክሮዎችን በመውሰድ እንዲጠቀሙበት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከግጭት አፈታት ውጪ ባሉ በተለያዩ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ 17 የምርምር ሥራዎች በዩኒቨርሲቲው በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም ዶ/ር ተስፋዬ ጠቁመው የሠላም ሚኒስቴርም እነዚህን ሀገር በቀል ዕሴቶች በደንብ ሊጠብቃቸውና የተለያዩ መድረኮችን ሊፈጥርላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ ሁሉም ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ዕሴት ያለው ሲሆን እነዚህንም ዕሴቶች ለዘላቂ ሠላምና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መጠቀም ልማት እንዲፋጠን፣ ዕድገት እንዲመጣ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ላይ ያሉ በርካታ ጉዳዮችን በማስቀረት ማኅበረሰቡ ትኩረቱን ልማት ላይ እንዲያደርግና አላስፈላጊ የሆነ የጊዜና የገንዘብ ብክነትን እንዲቀንስ የሚያስችል ግንዛቤ እንዲኖረው ይረዳል ብለዋል፡፡ ዕሴቶቹን በማጠናከርና በማደራጀት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋትም ተገቢ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የሀገር በቀል ዕውቀቶችና የባህል ሥርዓቶች ጥናትና  ምርምር ባለሙያ አቶ አብዱልፈታህ ሐምደላህ ‹‹የሀገር በቀል ባህል ሥርዓተ ማኅበራት ለግጭት መከላከልና መፍቻ ያላቸው መሠረትነት›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንደገለጹት የሀገር በቀል ባህል ሥርዓተ ማኅበራት ለግጭት መከላከልና መፍታት ያላቸው መሠረትነት ጥልቅና ሊነጣጠል  የማይችል ሆኖ ሳለ በዚያ ልክ ዕውቅና አልተሰጠውም ብለዋል፡፡  የሀገር በቀል ዕሴቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን እና ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ዕሴቶቹን ለመጠበቅ የትምህርት ሥርዓቱን መቀየርና ሳይንሳዊ ማድረግ እንዲሁም የመንግሥት ርዕዮተዓለም ማስተካከል እንደሚገባ በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡ በመጨረሻም በየተቋማቱ ውስጥ ለሚገቡ ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ የሆነና ሕይወታቸውን የሚጠብቁበት ነባራዊ ዕውቀትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን አቶ አብዱልፈታህ ተናግረዋል፡፡

‹‹ባህላዊ ተቋማት ሉላዊ በሆነው ዓለም ውስጥ እያጋጠማቸው ያሉ ፈተናዎች›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መ/ርና ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል መራዊ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ባህላዊ ተቋማት እያጋጠሟቸው ያሉ በርካታ ፈተናዎች እንዳሉና እነዚህም በተለያዩ ቡድኖች መካከል በማንነት ላይ ተመርኩዞ የሚካሄዱ ግጭቶችና ሌሎችም ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ መሰል ግጭቶችም ባህላዊ ተቋማት የቀድሞ ሥራቸውን እንዳይሠሩና በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን መፍታት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

በበሌላ በኩል ‹‹በደቡብ  ምዕራብ  ኢትዮጵያ በቆጎታ ወረዳ  የጋሞ  ባህላዊ ፍርድ ቤቶች (ዱቡሻዎች) በባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ውስጥ ያላቸው ሚና›› የሚለውን ጨምሮ በሀገር በቀል ባህሎች የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ላይ ያተኮሩ 18 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በአውደ ጥናቱም  ከሠላም ሚኒስቴር፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከሌሎች የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ ከደቡብ ክልል፣ ከጋሞ ዞን እና ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ተወክለው የመጡ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና የጋሞ አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ መ/ራንና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት