Print

"HUMAN BRiDGE" የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የሚሆኑ ዘመናዊና በሪሞት የሚሠሩ 240 የታካሚና የቀዶ ጥገና ክፍል አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ ዊልቸሮች፣ ክራንቾች፣ የቀዶ ጥገና ክፍል መብራቶች እና ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ሚያዝያ 22/2015 ዓ/ም ለሆስፒታሉ አስረክቧል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሂውማን ብሪጅ የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ አዳሙ አንለይ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ላስገነባው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ከተቋሙ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ድርጅቱ 240 የታካሚና የቀዶ ጥገና ክፍል አልጋዎች ከነፍራሾቻቸው፣ 12 የቀዶ ጥገና ክፍል መብራቶች፣ ክራንች፣ ዊልቸርና ሌሎች በገንዘብ ሲተመኑ 100 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በቅርቡም ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር የሚያግዙ የአልትራሳውንድ፣ የኦክስጅን ኮንሰንትሬሽን፣ የማዋለጃ አልጋዎችን እና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየሠራ እንዳለና አገልግሎቱንም ለማስጀመር የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ተገዝተው እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሰው ኃይል አንፃርም ለሆስፒታሉ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል መዋቅር ተሠርቶ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተላከ ሲሆን መዋቅሩ ጸድቆ ሲመጣ አስፈላጊው ቅጥር ይፈጸማልም ብለዋል፡፡ ከሂውማን ብሪጅ የተደረገው ድጋፍ ዩኒቨርሲቲውን ከከፍተኛ ወጪ የታደገና ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር ለሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ ይህም ድርጅቱን የሀገርና የዩኒቨርሲቲው ባለውለታ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ላዳረገውም ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡  

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ዩኒቨርሲቲው ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር የሲቲ ስካን ማሽንን ጨምሮ የኦክስጅን ፕላንት፣ የላውንደሪ ማሽኖች፣ የውሃ ማጣሪያዎች /Water Distillation/፣ የማዕድ ቤት ዕቃዎች፣ ማሽኖችና ሌሎች ቁሳቁሶች ግዢ ተፈጽሞ ገቢ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ወቅትም ለሆስፒታሉ የሚሆን 500 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ጨረታ ግዥ በመፈጸም ላይ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ታሪኳ  የሆስፒታሉ የመብራትና ውሃ መስመር ዝርጋታ ሥራ የተጠናቀቀ መሆኑን እንዲሁም የሆስፒታሉን ምድረ ግቢ ማስዋብ ሥራም በቅርቡ እንደሚጀመር  ገልጸዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ታሪኳ ገለጻ አሁን ላይ እንደ ሀገር ካለው የበጀትና የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትና ከሆስፒታሉ ግዙፍነት አንፃር ሆስፒታሉን በመንግሥት አቅም ብቻ ማሟላት ስለማይቻል ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ ለማግኘት በትኩረት እየሠራ ሲሆን ከሂውማን ብሪጅ የተገኘው ድጋፍም የዚሁ ጥረት ውጤት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በቶሎ ሥራ እንዲጀምር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ከተቋሙ አቅም በላይ በሆኑ ችግሮች ምክንያት በተባለው ጊዜ ሥራ ሳይጀመር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡  ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ለሆስፒታሉ ሥራ መጀመር አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችና ማሽኖች ተገዝተው ወደ ሆስፒታሉ የደረሱ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ታምሩ  በሂውማን ብሪጅ  የተገኙ ድጋፎች ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል፡፡  

ሆስፒታሉ 600 አልጋዎች ያሉትና ሌሎች በርካታ አገልግሎት መስጫ ከፍሎችን የያዘ ግዙፍ ተቋም መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ታምሩ በቀጣይ ከረጂ ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት የማጠናከርና በግዥ ሂዳት ላይ ያሉ ቁሳቁሶችን በአስቸኳይ እንዲገቡ የማድረግ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት